የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ እሴቶችን ሳይሸራረፉ በማቆየት ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ አባገዳዎች አስገንዝበዋል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ እሴት መገለጫ የሆኑትን እርቅ እና ሠላምን፣ ፍቅር እና አብሮነትን ለትውልድ ማስተላለፍ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አባ ገዳዎች አመላክተዋል፡፡
አባ ገዳ ለታ ቢራ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የተለያዩ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ማኅበራዊ እሴቶች ያሏቸው በመሆኑ ተከባብረውና ተቻችለው እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ የሚገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ባሕላዊና ማኅበራዊ አስተምህሮቶቻቸው ለእርቅ፣ ለሠላም፣ ለፍቅር እና ለአብሮነት ትልቅ ስፍራ የሚሰጡ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ መገለጫ የሆነው የገዳ ስርዓትንም ሆነ የኢሬቻ በዓልን ባህላዊ ክንዋኔውን ለተተኪው ትውልድ ይዘቱን ሳይለቅ ሊተላለፍ ይገባል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የወላጆች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያመላከቱት አባ ገዳ ለታ፣ አባቶች ልጆቻቸዉን በግልም ሆነ በዎል ባህላዊ እና ማህበራዊ እሴቶችን በማስተማር የድርሻቸዉን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ እርስ በርሱም ሆነ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የሚኖረውን መስተጋብር ይበልጥ ከማጠናከር ባለፈ ለመጪው ትውልድ እሴቶቹ ሳይበረዙ ማስረከብ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የኢሬቻ በዓልም እነዚህን እሴቶች በማጠናከርም ሆነ ለትውልድ በማስተላለፍ የሚኖረው አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ስለሆነ የዘንድሮም በዓል በዚሁ አግባብ እንዲከበር አባገዳዎች ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በፍሬሕይወት ብርሃኑ