በኢሬቻ ዙሪያ በአለም አቀፍ ጆርናሎች የተሰራጩ ጥናቶች ስለ በዓሉ እና አከባበሩ ምን ይላሉ?

You are currently viewing በኢሬቻ ዙሪያ በአለም አቀፍ ጆርናሎች የተሰራጩ ጥናቶች ስለ በዓሉ እና አከባበሩ ምን ይላሉ?

AMN-መስከረም 24/2018 ዓ.ም

የኢሬቻን ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ማኅበራዊ ገጽታዎች በስፋት የሚዳስሱ በበዓሉ ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች አሉ።

እነዚህ ጽሁፎች እና ጥናቶች አለም አቀፍ ጥናቶችን በሚሸፍነው ሚድዊን ፐብሊሸርን ጨምሮ በአፍሪካ ፕረስ መጽሄት ላይ ሰፊ ሽፋንን አግኝተዋል።

የሀረማያ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ልማት ጥናት ተቋም ባልደረባ መገርሳ ቶሌራ (Irreechaa: Unveiling the Multidimensional Significance of a Cultural Phenomenon) በሚል ርዕስ የጻፉት በሜድዊን ፐብሊሸር ላይ የወጣው የጥናት ጽሁፍ፤ ኢሬቻ የኦሮሞ ማህበረሰብ መገለጫ እንደሆነ ያስቀምጠዋል።

ጽሁፉ ሲቀጥል፤ ኢሬቻ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በየዓመቱ በመስከረም ወር የሚከበር ታላቅ የምስጋናና የሰላም በዓል እንደሆነ ይናገራል።

ይህ በዓል ለዘመናት ሲከበር የኖረ ሲሆን፤ ለኦሮሞ ሕዝብ ልዩ ታሪካዊ እና ባህላዊና ትርጉም እንዳለው፤ የኦሮሞ ሕዝብ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን የጠበቀ ግንኙነት የሚያሳይ ልዩ ሥነ-ሥርዓት እንደሆነም ያክላል።

ክብረ በዓሉ ተፈጥሮ እና ፈጣሪ በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ስላላቸው ዋጋ ከፍተኛ እውቅና እንደሚሰጥ የሚያመላክተው ጽሁፉ፤ ከክረምት (ጨለማ ወራት) በኋላ ወደ ፀደይ (ብራ) ወቅት በሚደረገው ሽግግር ላይ ለሰላም፣ ለጤና፣ ለእርሻ ምርትና ለከብቶች ብዛት፣ እንዲሁም ለተገኘው ነገር ሁሉ ፈጣሪን ለማመስገን የሚውል እንደሆነ ያትታል።

በገብረአብ ደመቀ ዋቀዮ ተጽፎ በአፍሪካን ፕረስ መጽሔት ላይ (The Oromo Thanksgiving (Irreechaa) and the Reemergence a God Fearing Ancient Republican Polity) በሚል ርእስ የወጣው መጣጥፍ በበኩሉ፤ ኢሬቻ የኦሮሞ ማህበረሰብ ፈጣሪን ምን ያህል እንደሚያከብር ገላጭ መሆኑን ይጠቅሳል።

በተጨማሪም በዓሉ ከኢትዮጵያ አልፎ በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በሚኖሩ የኦሮሞ ማህበረሰቦች እንደሚከበር ይገልጻል።

በአሉን የኅብረትና የሰላም ምልክት አድርጎ የሚያነሳሳው ይህ ጽሁፍ፤ ኢሬቻ የኦሮሞን ሕዝብ ከተለያዩ የሃይማኖትና የፖለቲካ አስተሳሰቦች ባሻገር አንድ የሚያደርግ የጋራ መድረክ ነው ይለዋል።

በዓሉ ህዝቦች በሰላም፣ በመከባበርና በጋራ ማንነት ዙሪያ እንዲሰባሰቡ ዕድል እንደሚሰጥም ይናገራል።

በኢሬቻ አከባበር ስነ-ስርአት ወቅት ሰዎች አረንጓዴ የሳር ቅጠልና አበባ በመያዝ ወደ ወንዝ ወይም ሐይቅ ዳርቻ በመሄድ፣ በውሃ ውስጥ በመንከር ለፈጣሪ ምስጋና ያቀርባሉ፤ ይህም የባህል መገለጫ እና የማንነት ማጠናከሪያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ነው የሚያብራራው።

የሀረማያ ዩኒቨርስቲ የሰላም እና ልማት ጥናት ተቋም ባልደረባ መገርሳ ቶሌራ ተጽፎ በሜድዊን ፐብሊሸር ላይ ወደ ተሰራጨው የጥናት ጽሁፍ ስንመለስ ፤ ኢሬቻ የምስጋና በዓል ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የኦሮሞን ሕዝብ ባህልና ማንነት የሚያጠናክር ማኅበራዊ መድረክ ስለመሆኑ ተጽፎ እናገኛለን።

በበዓሉ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች በባህላዊ የኦሮሞ ልብሶች ያጌጣሉ፤ በልብሶቹ ላይ የሚሰሩ ጥልፎችና ዲዛይኖች የኦሮሞን ገጽታ፣ ታሪክና እሴቶችን የሚገልጹ ናቸው።

ኢሬቻ በሕዝቡ መካከል ሰላምን፣ መተባበርን እና አብሮነትን ከማጉላት በዘለለ ለወጣቱ ትውልድ የኦሮሞን ባህል፣ ወግና ታሪክ የሚያስተምርበትም ነው ይላል።

ጽሁፉ በማጠቃለያው ይህ ማህበረሰባዊ እና ሀገራዊ ፋይዳው ግዙፍ የሆነ በዓል ጥልቅ ምርምር እና ጥናት እንደሚይስፈልገው ይጠቁማል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review