ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት “ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ” የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ እና የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን ስምምነቱን በቤልጂየም ብራሰልስ መፈራረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ባለው የረጅም ጊዜ አጋርነት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነም ተገልጿል።
“ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ” በአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን የሚመራ የአውሮፓ ህብረት ዓለም አቀፍ ኢኒሼቲቭ ሲሆን ህብረቱ ከተለያዩ ሀገራት በዲጂታላይዜሽን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በስርዓተ ምግብ፣ በጤና፣ በዘላቂ ግብርና፣ በሰላም እና ደህንነትን ጨምሮ በቁልፍ ዘርፎች ያለውን ትብብር እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነው።
ከስምምነቱ በፊት ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ፍላጎታቸውን መሰረት አድርገው ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከርና ለማስፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ “ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ የጋራ ስትራቴጂካዊ ራዕይን ለማሳካትና የኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት አጋርነት በማይበገር ሁኔታ መገንባት የሚያስችል ጊዜውን የጠበቀ ስምምነት መሆኑን ገልጸዋል።
የትብብር ስምምነቱ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የዲፕሎማሲ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ ትልቅ እርምጃ መሆኑም አክለዋል።
ሁለቱ ወገኖች እ.አ.አ በ2016 ለተፈራረሙት የስትራቴጂክ ትስስር የጋራ ድንጋጌ አዲስ አቅም እንደሚፈጥርም ተመላክቷል።