ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ረቡዕ በሀላባ እና ከምባታ ዞኖች የነበረንን የሞዴል የገጠር መንደሮች ርክክብ ሥነሥርዓት በመቀጠል ዛሬ ደግሞ በሀዲያ እና ስልጤ ዞኖች የተገነቡትን አስረክበናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እነኚህ ባለሶስት መኝታ ቤት መኖሪያዎች ለማብሰል የሚያገለግል የባዮጋዝ መሣሪያ፣ የፀኃይ ኃይል ማመንጫ፣ የዶሮ ማርቢያ፣ የተለየ የእንስሳት በረት የተሟላላቸው ሲሆን በተመጣጣኝ አነስተኛ ወጪ ከአካባቢ በሚገኙ ግብዓቶች የተሻለ መኖሪያ ከማስገኘት አንፃር ለገጠሩ ማኅበረሰብ ብልጽግና ያለንን ሕልም የሚያሳይ ነው።

እንደ ማኅበረሰብ አዲስ ሀሳቦች ሲፈልቁ “አይቻልም” በሚለው የቆየ አስተሳሰብ የመፈተን ተግዳሮት ይደቀንብን ይሆናል። ይሁንና በተጨባጭ በሚታየውና በተገኘ ውጤት ላይ ወደ አለማመን እና አለመቀበል በሚመራን የሀሳብ ወጥመድ ውስጥ መውደቅ የለብንም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዜጎች ለውጥ እንደሚቻል ሀብቶቻችንን ወደ ትክክለኛ የቅድሚያ ትኩረቶቻችን ካዋልንም ማኅበረሰብን በርግጥም ማሻገር እንደምንችል ማመን ይገባቸዋል። በአራቱ ዞኖች የተሠራው ሥራ በመላው ክልሉ መደገም ይኖርበታል። የክልሉ አመራር ይኽን ታላቅ ስራ እንደሚፈጽመውም እምነት ጥያለሁ በማለት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡