የሳውዲ አረቢያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት የኢትዮጵያን መልካም ገፆታ ለመላው ዓለም በማስተዋወቅ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገልጿል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሳዑዲ አረቢያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላትን ተቀብሎ አወያይቷል፡፡
በውይይቱም የሳውዲ አረቢያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ በመወከል ታዋቂ ሰዎች፣ ባለሀብቶች እና የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ትስስርና አሁናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነትና በተጨማሪም የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ ለመገንባት የሚያስችሉ ጉዳዮች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የኢትዮ – ምዕራብ እስያ ወዳጅነት ቡድን ሰብሳቢ ሙሐመድ አል አሩሲ ኢትዮጵያ እና ሳውዲ አረቢያ ረጅም ዓመታትን ያሰቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት እና የጋራ ባህል አንዳላቸው አውስተው፣ ሁለቱ ሀገራት ከሁለትዮሽ ግንኙነት በተጨማሪ በባለብዙ ወገን ትብብርን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በርካታ የሳውዲ አረቢያ ዜጎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራታቸውን ጠቁመው፣ የሁለቱ ሀገራት ትብብርና ወዳጅነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን መግለፃቸውንም ምክር ቤቱ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ ገልጿል፡፡
አክለውም ኢትዮጵያ እንደ ታላቁ ሕዳሴ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ገንብታ በማጠናቀቅ ለውጥ እያመጣች ነው ያሉ ሲሆን የግድቡን ጠቀሜታ አንድታስተዋውቁ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የኢትዮ – ምዕራብ እስያ ወዳጅነት ቡድን አባል ወ/ሮ መስከረም ኃይሉ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ እና በሳውዲ አረቢያ መካካል ያለው ግንኙነት አበረታች መሆኑን ጠቁመው፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላቱ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በጋራ የራስ ጥረትና ትብብር ግንባታው ተጠናቆ በተመረቀበት ማግስት በመሆኑ ልዩ አንደሚያደርገው ገልፀዋል፡፡
አያይዘውም ኢትዮጵያ በልማቱ በኩል በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እያመጣች መሆኑን ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ አስገንዝበዋል፡፡