በአዲስ መሶብ በ13 ተቋማት 107 አገልግሎቶች ይሰጣሉ
አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ማስጀመር፣ ማስገንባት እና አጠናቅቆ ለአገልግሎት ማብቃትን የዕለት ተዕለት ተግባሩ ያደረገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ የሥራዎቹ ውጤቶች ለውጥ ማምጣት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ የፕሮጀክቶቹ ዓይነት፣ ብዛት፣ ፋይዳ፣ መጠን… የተለያየ ቢሆንም፤ የመዳረሻ ግባቸው ግን አንድ እና አንድ ነው፡፡ ከተማዋን ዘመናዊ፣ ውብ፣ ፅዱ እና ዓለም አቀፍ ደረጃዋን በማስጠበቅ ለነዋሪዎቿ እና ለእንግዶቿ የተመቸች ማድረግ ነው፡፡ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ፕሮጀክቶቹ ከመሰረተ ልማት ግንባታ ባሻገር፣ ለቴክኖሎጂ እና ለሠው ሀብት ልማት ትልቅ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ ምክንያቱም የተገነቡት ውብ እና ዘመናዊ መሰረተ ልማቶች፣ የተሟሉት ዘመኑን የዋጁ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች፣ በየተቋማቱ የተሠማራው በዕውቀትና በክህሎት የዳበረ የሠው ኃይል ተቀናጅተው ለህብረተሰቡ እርካታ የሚፈጥር አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ አለባቸው፡፡
ከሰሞኑ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት፤ ከላይ ያነሳነውን “የነዋሪውን ህብረተሰብ የአገልግሎት እርካታ ደረጃ ከፍ የማድረግ ዓላማ” ለማሳካት እንደከተማ አስተዳደር እየተሠሩ ያሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ለማስረዳት ጥሩ አብነት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ የአዲስ መሶብ ማዕከል ዋና መሥሪያ ቤቱን በቀድሞው የአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሕንጻ ላይ አድርጓል፡፡ በዝግጅት ምዕራፉ ለአገልግሎት አሰጣጡ ስኬት የሚያግዙ ተቋማዊ የቤት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ነባሩን ሕንጻ፤ ለአገልጋይም ሆነ ለተገልጋይ በሚመች መልኩ ታድሷል። አስፈላጊ የሆኑ ዘመናዊ እና የረቀቁ አገልግሎትን አሳላጭ ቴክኖሎጂዎች ተሟልተውለታል፡፡ ተመሳሳይ የሥራ ልብስ ለብሰው በየወንበራቸው የተሰየሙ ወጣት ባለሙያ እና አመራሮች ለማገልገል ያላቸው ዝግጁነት ከገጽታቸው ይነበባል። በአዲሱ ተቋም የተጀመረው የሥራ ባህል ነገና ከነገ ወዲያ ፍሬውን ለማየት ያጓጓል።

በምልከታችን ታዝበን፣ ለሚያመጣው ውጤት የጓጓንለት ለአገልግሎት አሰጣጥ ያለውን ዝግጁነት (በተለይም ከቴክኖሎጂ ግብዓት ጋር የተያያዘውን) በተመለከተ በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁን አነጋግረናቸዋል። እሳቸው በሰጡት ማብራሪያ “ማዕከሉ አገልግሎቱን የሚጀምረው በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ የመንግስት ተቋማት መካከል 13 (አስራ ሦስት) የሚሆኑትን አገልግሎት በማሰባሰብና በማቀናጀት ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት፡- መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን፣ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ ንግድ ቢሮ፣ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ባለስልጣን፣ የመሬት ይዞታና ምዝገባ መረጃ ኤጀንሲ፣ የሲቪል ምዝገባና ነዋሪዎች አገልግሎት ቢሮ፣ የሥራና ክህሎት ቢሮ፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ገቢዎች ቢሮ፣ ግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን እንዲሁም ፕላንና ልማት ቢሮ ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ፤ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የስኬት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የመሳሰሉ የፌዴራል ተቋማትም በማዕከሉ አገልግሎታቸውን ይሰጣሉ፡፡ የተቋማቱን የተናጥል ወይም የተቀናጀ አገልግሎት ፈጣን፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ በሆነ አግባብ ለተገልጋዩ ማድረስ የማዕከሉ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ከሚያግዙ አቅሞች ውስጥ ደግሞ አንደኛው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ማዕከሉ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀማል፡፡”
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አክለው እንደገለፁት፤ “ማዕከሉ ከመግቢያ በር እስከ ውስጠኛው አገልግሎት እስከሚሰጥባቸው ድረስ ያሉት ክፍሎች በቴክኖሎጂ ግብዓት ተሟልቷል፡፡ ቀደም ሲል በተለያየ ቦታ፣ በበርካታ የሰው ኃይል፣ በተበጣጠሰ መልኩ ይሰጡ የነበሩ የተለያዩ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል ለመስጠት የሚያስችል የመተግበሪያ(አፕሊኬሽን) ለአገልግሎት በቅቷል፡፡ ይህ መተገበሪያ በሀገር ውስጥ አቅም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የለማ ሲሆን፤ የየተቋማቱን አገልግሎቶች ወደ አንድ በማሰባሰብ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት አገልግሎቶችን ለተገልጋዮች ያደርሳል፡፡”
ተገልጋዮች ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው ወደ ማዕከሉ እስከመጡ ድረስ፤ ፈጣን፣ ቀለልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢ የሆነ እና የተገልጋይን እርካታ የጨመረ አገልግሎት ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ እንደሆኑ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በማዕከሉ አገልግሎታቸውን ያቀረቡት ተቋማት ከዚህ ቀደም በየተቋሞቻቸው የዲጂታል አገልግሎትን የጀመሩና ሲተገብሩ የቆዩ መሆናቸውን አንስተዋል። ማዕከሉም የእነዚህን ተቋማት የዲጂታል አገልግሎት በአንድ ቦታና በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ማቅረብ የሚያስችልን መተግበሪያ (ፕላትፎርም) በመጠቀም የተሰጠውን ኃላፊነት ይወጣልም ብለዋል፡፡ ዘመናዊው የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያው፤ የትኛው ሠራተኛ ምን ያህል አገልግሎት እንደሰጠ፣ ስንት ተገልጋይ በየትኛው ክፍል ውስጥ አገልግሎት እንዳገኘ፣ አገልግሎቱን በምን ያህል ሰዓት እና ቀን ውስጥ እንዳገኘ፣ የትኞቹ አገልግሎቶች በስፋት እንደተሰጡ እንዲሁም የደንበኛው እርካታ ደረጃን የሚለካ ስለመሆኑም ገልጸውልናል፡፡

ማዕከሉ እንደተቋም አሁን ያለበትን ገፅታ እንዲላበስ፣ የሥራ ዝግጁነቱ እንዲሟላ፣ ለአገልግሎትም እንዲበቃ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ካደረጉለት ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ አንዱ ነው፡፡ ቢሮው ለማዕከሉ እውን መሆን ያደረገው አስተዋፅኦ፤ እንደተቋም የተሰጠውን ተልዕኮ እንደፈፀመ ተደርጎ የሚወሰድ ቢሆንም፤ እንዲህ ዓይነት አዳዲስና ዘመናዊ አሠራሮች ዕውን የሚደረጉበትን የተለየ እንቅስቃሴ ማድነቅ ደግሞ ይገባል።
አቶ አዋሌ መሀመድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ናቸው፡፡ የዝግጅት ክፍሉ ከእሳቸው ጋር በነበረው ቆይታ፤ በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎትን የተመለከቱና ከዚህ ጋር የተያያዙ ሃሳቦችን አጋርተውናል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፤ አዲስ መሶብ ከዚሀ ቀደም በተለያዩ ተቋማት ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ በአንድ መስኮት እንዲሰጥ የሚያደርግ የአሠራር ስርዓት ነው። በአዲስ መሶብ የተሳሰሩ ተቋማት እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን ዳታቤዝ እና ሲስተም ይዘው በመምጣት በአዲስ መሶብ ማዕከል ውስጥ ትስስር ፈጥረው አገልግሎታቸው በተናጥል ወይም በተቀናጀ መልኩ ያደርሳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በተናጥል ሲተገበሩ የነበሩ የየተቋማቱ ዘመናዊ የአሠራር ስርዓት መተግበሪያዎች (አፕሊኬሽኖች) አንድ ላይ በማስተሳሰር ብዙ አገልግሎቶችን በአንድ መስኮት ወይንም በአንድ ቦታ የሚሰጥበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ይህም የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል በሚል ይጠራል፡፡
በመዲናዋ ያሉ የመንግስት ተቋማት ተልዕኮዎቻቸውን ለህብረተሰቡ ተደራሸ ለማድረግ እንዲሁም ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና ፍትሀዊ አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ያስታወሱት አቶ አዋሌ፤ በተሠሩት ሥራዎች እንደከተማ ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ከ347 በላይ የሚሆኑ አገልግሎቶችን ዲታላይዝ በማድረግ በኦንላየን መስጠት መቻሉን አብራርተዋል፡፡ ከጳጉሜ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለአገልግሎት የበቃው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት የዚህ ሥራ ዕድገት ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎትን አስመልክቶ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊው አቶ አዋሌ እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡ “በማዕከሉ አገልግሎታቸውን መስጠት የጀመሩት ተቋማት ትስስር በመፍጠር 107 የሚሆኑ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በታገዘ ሁኔታ ኦንላይን ይሠጣሉ፡፡ ይህም ቀደም ሲል በተበጣጠሰ ሁኔታ ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን ወደ አንድ ማእከል በማምጣት ህብረተሰቡ ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል፡፡” የቢሮ ኃላፊው አያይዘው፤ “ቴክኖሎጂውን የሚተገብሩ ባለሙያዎችን በማብቃት ረገድ ፊት ለፊት አገልግሎቱን ከሚሰጡት ጀምሮ ሲስተሙ እንዳይቆራረጥ የሚያደርጉ የተለያዩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ የባለሙያዎቹን ብቃት በማሳደግ ረገድ የኢትዮ ኮደርስን ስልጠናን እንዲወስዱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ በከተማዋ ከ400 ሺህ በላይ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ከ220 ሺህ በላይ ስልጠናውን አጠናቅቀዋል፡፡ ሌላው በአዲስ መሶብ እንዲያገለግሉ ለተቀጠሩ ባለሙያዎች ከስራቸው ጋር ተዛማጅነት ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ስልጠና ተሰጥቷል። ህብረተሰቡም ይህንን በአዲስ መልክ የተጀመረውን አዲስ መሶብ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አገልግሎት የማስተዋወቅና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ ነው። የአገልግሎቱን መጀመር ለማስተዋወቅ የተጠቀመበት ሌላው መንገድ የቢሮው ፖርታል ዌብሳይት ነው፡፡”
የሲስተም መቆራረጥ እንዳያጋጥም ምን ታስቧል? ሲልም የዝግጅት ክፍሉ ላነሳላቸው ጥያቄም ቢሮ ኃላፊው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በምላሻቸውም፤ “ድግግሞሽ ባለው መንገድ ነው የሚሰራው፡፡ ሪደንደንት(ድግግሞሽ) ማለት በምንም መልኩ የሲስተም መቆራረጥ እንዳያጋጥም የሚያደርግ አሰራር ነው፡፡ ለምሳሌ፤ በቀጥታ ስራው ከሚሰራበት ዳታቤዝ ሌላ ተጨማሪ ዳታ ቤዝ ተዘጋጅቷል፡፡ ሌላው የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ ሲስተሙን እንዳይቆራረጥ የመብራት መስመሩን ሁለት ማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ አንዱ ቢቋረጥ ወደሌላው ማዞር፡፡ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመውን መቆራረጥም በተመሳሳይ የተለያየ መስመር በመዘርጋት መከላከል ነው፡፡ እንዲህ አይነት የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ያስፈለገበት ዓላማ ችግሮች ሲያጋጥሙ በቀላሉ ከችግር መውጣት እንዲቻል ለማድረግ ነው፡፡”
አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በማዘመን ተገልጋይ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ በማስቻል ረገድ ቀጣይ የቢሮው እቅድ ምን ይሆን? ሲልም የዝግጅት ክፍሉ ቢሮ ኃላፊውን አቶ አወሌን ጠይቋቸዋል፡፡ “እንደሳቸው ገለጻ፤ ቢሮው የተገልጋይን እምባ ማበስ ነው፡፡ የተገልጋይን እምባ የሚያብሱ ሲስተሞችን ማልማት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር 75 የሚሆኑ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ወደ አንድ ቋት ወይንም ማእከል እንዲመጡ አቅዷል፡፡ በተለይም የህብረተሰብ እሮሮ የሚሰማባቸውን እና እንግልት ያለባቸውን አገልግሎቶች በማቃለል በአገልግሎት አሰጣጡ እርካታ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ልየታ ተደርጓል፡፡

ከዚህ አንጻር ቀደም ሲል የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አንዱ ነዋሪዎች ቅሬታ የሚያነሱበት ተቋም ነው፡፡ የነዋሪዎችን ቅሬታ ለመፍታትም የተቋሙን የአገልግሎት ሲስተም በማሳደግ አገልግሎቱን ማሻሻል አንዱ እቅድ ነው፡፡ ከመሬት አገልግሎት ጋር ተያይዞም ይነሳ የነበረውን ሰፊ ችግር ለመፍታት የአገልግሎት አሰጣጡን ሙሉ በሙሉ ኦንላይን ለማድረግ ታቅዷል። ከዚህም በተጨማሪ የአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ እንዲሆን ህብረተሰቡን የሚያሳትፍ ስርዓት እየተገነባ ነው። ለምሳሌ የኮሪደር ልማቱን ያለአግባብ ለመጠቀም የሚሞክሩትን ለመከላከል የሚያስችል ሲስተም ነው፡፡ የከነማ ፋርማሲ ፍትሀዊ ያልሆነ የመድሀኒት አጠቃቀም ችግርን በማስቀረት ረገድም ሌላው በእቅድ የተያዘው ተግባር ነው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ከህብረተሰቡ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው አገልግሎቶች ማልማት ነው የቢሮው የትኩረት አቅጣጫ፡፡”
መቀመጫውን በአራዳ ክፍለ ከተማ የቀድሞ ሕንፃ ላይ በማድረግ አገልግሎቱን በይፋ የጀመረው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት፤ በቀጣይ ቅርንጫፎችን በመክፈት ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደሚሠራ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪነት በቦሌ ክፍለ ከተማ እና በአካባቢው ላሉ ነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ዝግጁ የሆነው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት፤ በቅርቡ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም የቅርንጫፎቹን ቁጥር አስር ለማድረስ በዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል፡፡
በለይላ መሀመድ