የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዩናይት ኪንግደምና የአካባቢው አውሮፓ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎችን ለማስመረጥ በለንደን ያዘጋጀው መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ በምክክር መድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎችን በኮሚሽኑ ስም አመስግነዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክሩ ባለቤቶች ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ናቸው ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ የኮሚሽኑ ራዕይ ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር ሰላማዊና ዴሞክራሲዊት ኢትዮጵያዊ ዕውን እንድትሆን መሠረት መጣል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም አካታች ምክክር ለማድረግ ብዙዎች ሲጠይቁ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ያለው ትውልድ ይህንን ታሪካዊ የመመካከር ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
ኮሚሽኑ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ተግባራት እንዳከናወነ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ፤ እስካሁን ድረስ ሁሉን አካታች የሆኑ የምክክር መድረኮች በመላው ኢትዮጵያና በተለያዩ የውጪ ሀገራት መከናወናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከሕዝባዊ መድረኮች በተጨማሪ ተቋማትና ግለሰቦች አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ እያስረከቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የምክክር ሂደቱን በተመለከተ ሰፊ ግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም አክለዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የነፃነት ቀንዲል የሆነችውን ሀገራችንን የመቻል አቅም የሚያሳይ ስለሚሆን፤ ሁሉም ዜጋ ሂደቱን ሊደግፍ እንደሚገባም ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመክፈቻ መድረኩ ላይ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) የኮሚሽኑን የእስካሁን የስራ እንቅስቃሴ፣ የሀገራዊ ምክክር ምንነት፣ አሰፈላጊነትና የምክክር ስነ ዘዴዎችን በተመለከተ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
የምክክሩ ተሳታፊዎች ስለ ኮሚሽኑ፣ ስለ ምክክሩ ሂደትና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ያሏቸውን ጥያቄዎችና አስተያየቶችን በመድረኩ ለተገኙ ኮሚሽነሮች በማቅረብ ላይ መሆናቸዉን ኮሚሽኑ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡