ጥቅምት 4/2005 የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መስራች ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ከመድረኩ ከራቀች 31 ዓመት በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የሆነችበት ዕለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ይህን ታሪካዊ ድል ያስመዘገበችው ከሱዳን ጋር ባደረገችው የደርሶ መልስ ጨዋታ ነበር፡፡ ሱዳን ላይ 5ለ3 የተሸነፉት ዋልያዎቹ አዲስ አበባ ላይ 2ለ0 ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡
ከሜዳ ውጪ ብዙ ባገባ በሚል ባለድል የሆነችበት ዕለት አዲሱ ትውልድ የተመለከተው ትልቁ የእግርኳስ ስኬት ሆኖ አልፏል፡፡ ጥቅምት 4/2005 በመላው ኢትዮጵያ የነበረው ደስታ ልዩ ነበር፡፡
ከ31 ዓመት በኋላ ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመሩ የተወዳደሩት ዋልያዎቹ ምድባቸውን ባያልፉም ተሳትፎአቸው ብቻ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ አንድ ጊዜ ብቻ የአፍሪካ ዋንጫ መድረክ ላይ ተገኝታለች፡፡ አሁን ያለው ብሔራዊ ቡድንም ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚያስችል ቁመና ላይ አይደለም፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ