የኢትዮጵያ ሕልውና እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ከቀይ ባሕርና ከዓባይ ተፋሰስ ጋር የተሰናሰለ መሆኑ ተገለፀ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ሕልውና እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ከቀይ ባሕርና ከዓባይ ተፋሰስ ጋር የተሰናሰለ መሆኑ ተገለፀ

AMN – ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሕልውና እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ከቀይ ባሕርና ዓባይ ተፋሰስ ልማት ጋር የተሰናሰለ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ገለጹ።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ በመከላከያ ዋር ኮሌጅና በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ትብብር “የሁለቱ የውሃ ሥርዓቶችና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ነፃነት፣ የዓባይና የቀይ ባሕር ትስስር እና የአፋር ክልልን ስትራቴጂካዊ ሚና መዳሰስ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ምክክር እየተካሄደ ይገኛል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፥ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት፣ የስልጡን ህዝቦችና አርበኞች ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ ከዓባይ ሸለቆና ከቀይ ባሕር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላትና የአፍሪካ ቀንድ አስኳል መሆኗን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሕልውና እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ከቀይ ባሕርና ከዓባይ ተፋሰስ ልማት ጋር የተሰናሰለ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የጂኦፖለቲካዊ እሳቤም ከሁለቱ የውሃ አካላት ጋር የሚቃኝ መሆኑን በማንሳት፥ ወደ ቀይ ባሕር ስንቀርብ ኃያልነታችንና እሳቤያችን ይሰፋል ብለዋል።

ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ያህል ጂኦፖለቲካዊ በሆነው ስለ ቀይ ባሕርም ሆነ ስለባሕር በር ጉዳይ ምርምርና የፖሊሲ ውይይት ማካሄድ ፈጽሞ የማይታሰብ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያን የቁጭት ዘመን ምላሽ ለመስጠት መንግሥት ስለ ባሕር በር መነጋገር እንደነውር የሚቆጠርበት ዘመን እንዲያከትም ማድረጉን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

“የሁለቱ ውሃዎች እና የኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ነፃነት” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው ኮንፈረንስም ሁለቱን ውሃዎች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የእለት ተዕለት አጀንዳ ማድረግ በማስፈለጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ከባሕሩ ባሻገር ከራስ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ እውነት እና ሥነ-ልቦና ጋር መታረቅ ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መሀመድ ዑስማን(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር በርን የማግኘት ፍላጎትም ከታሪክ፣ ጂኦግራፊና ቀጣናዊ ደኅንነት ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ኮሞዶር ተገኝ ለታ፥ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብሔራዊ ተጠቃሚነት ከዓባይና ከቀይ ባሕር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ብለዋል።

ከበርካታ ዓመታት በፊት ፈርሶ የነበረውን የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መልሶ በማደራጀት በሰው ኃይል፣ በአደረጃጀት፣ በቴክኖሎጂ አስተማማኝና ጠንካራ ሠራዊት እየተገነባ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review