የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የባህር በርን ጨምሮ ቀሪ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ስብራቶችን ለመጠገን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትጋት እንደሚሰራ ገለጸ።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮችና የፓርቲ አጀንዳዎች ላይ መክሮ አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልጸዋል።
ፓርቲው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና የማረጋገጥ ራዕይን ሰንቆ ወደ ተግባር መግባቱን አውስተው፤ ባለፉት ዓመታት ለህዝብ ቃል የገባውን በውጤታማነት እየፈጸመ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ቀሪ ስብራቶች ለመጠገን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትጋት እንደሚሰራ ተናግረው፤ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረጉ የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ገልፀዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት በተሠሩ የልማት ስራዎች ከፍተኛ ውጤት መምጣቱን ገልጸው፤ ለአብነትም ባለፈው ዓመት የ9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እየተረጋገጠ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው መገምገሙን ጠቅሰው፤ በዚህም ኢኮኖሚው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪና ዘመናዊ አገልግሎት እየተሸጋገረ ይገኛል ብለዋል።
በገቢ ማሰባሰብ፣ በወጭ ንግድ እና በተኪ ምርት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን በማንሳት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ፈጣን ብቻ ሳይሆን አካታች፣ ጥራት ያለውና የህዝቡን ኑሮ በተጨባጭ እያሻሻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በተጀመሩ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸው፤ በሰው ተኮር ስራዎችም በርካታ አቅመ ደካማ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይም ተረጂነትን የማስወገድ፣ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት በቂ ፈንድ የመያዝ እንዲሁም ብሄራዊ የመጠባበቂያ ክምችትን በራስ አቅም የማምረት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሰላም እና የፖለቲካ ጉዳዮችን መገምገሙን በማንሳት ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የበኩሉን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑን ማረጋገጡን ጠቅሰዋል።
መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተአማኒ፣ ግልጽና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ፓርቲው የድርሻውን እንደሚወጣም ገልጸዋል።
ውስን የሰላምና ፀጥታ ችግር የነበረባቸውን አካባቢዎችን ለማረጋጋት መንግስትና ህዝብ በጋራ በሰሩት ስራ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
ማንኛውም የፖለቲካ ጥያቄ ያለው አካል ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ምህዳር መፈጠሩን ገልጸው፤ ፓርቲውና የሚመራው መንግስት ሁልጊዜም በራቸው ለሰላም ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።
በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ለማድረግ የተቀመጠው አቅጣጫ ወደ ተጨባጭ ተግባር መገባቱን ተገምግሟል ብለዋል።
በዚህም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የማስፋትና የዲጂታላይዜሽን ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን አመልክተው፤ እስካሁንም 16 ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሠጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመሶብ ማዕከላት የህዝቡ እርካታ ወደ 95 መቶ መድረሱን ገልጸው፤ የመሶብ ማዕከላትን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓም ወደ መቶ ለማድረስ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ጠንካራ መንግስትና ሀገር ለመገንባት የያዘውን ግብ ለማሳካት የአመራርና አባላቱን አቅም የሚያጎለብቱ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑንም ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ አመራርና አባላቱ በተሠጣቸው ተልዕኮ ልክ በየደረጃው የመገምገም ስራ ሲሠራ መቆየቱን ጠቁመው፤ በምዘናው መሠረት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡት እውቅና መሰጠቱን መጥቀሳቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል የተሰጣቸውን ሀገራዊና የፓርቲ ተልዕኮ በአግባቡ ባልተወጡ አመራሮች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን መወሰዱን ተናግረው፤ ፓርቲው ህዝብና ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመራችውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።