የኮሪደር ልማቱ ለንግድ ሥራቸው ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላቸው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ

You are currently viewing የኮሪደር ልማቱ ለንግድ ሥራቸው ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላቸው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ

AMN- ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም

የኮሪደር ልማቱ ለንግድ ሥራቸው አመቺ የሆነ ስነ-ምህዳር እንደፈጠረላቸው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ጽዱነት፣ ውበት እና ለነዋሪዎች ምቹ መሆን የአዲስ አበባ ከተማ መገለጫዎች እየሆኑ መጥተዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ደግሞ በተለይ ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ለንግድ ተቋማት ምቹ መደላድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡

እንደነዚህ አይነት መሰረተ ልማቶች መሰራታቸው ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ገልጸዋል፡፡

ወጣት ሮቤል ዘመኑ በአልባሳት ስፌት እና ሽያጭ ሥራ ላይ የተሰማራ ሲሆን፣ የኮሪደር ልማቱ ለደንበኞች ያዘጋጃቸውን አልባሳት ባማረ ስፍራ ላይ ማቅረብ እንዳስቻለው እና ምርቶቹ እንዲታዩም ዕድል መፍጠሩን ተናግሯል፡፡

ልብስ ለማሰፋት ሀሳብ የሌለው ሰው እንኳን እንደዚህ በግልጽ አዳዲስ ሥራዎችን ሲያይ ለማዘዝ ሊወስን እንደሚችል ነው የገለጸው፡፡

በዚህ መልኩ አምሮ እና ተውቦ በተሰራ ቆንጆ ሥፍራ ላይ በሚገኝ ሱቅ የተሰሩ ስራዎችን ለዕይታ ማቅረብ ደንበኞችን እንደሚስብም አመላክቷል፡፡

በሌላ ጠባብ እና መንቀሳቀሻ በሌለው ቦታ ላይ መስራት በራሱ የሚፈጥረው ድብርት እንዳለ ያነሳው ወጣት ሮቤል፣ እንደዚህ ያለ ቦታ ግን የሥራ ከባቢውንም የተሸለ እንደሚያደርገው ነው የተናገረው፡፡

በአልባሳት ንግድ ሥራ ላይ ያለችው ሌላኛዋ ወጣት ቃልኪዳን ገዛኸኝ፣ የኮሪደር ልማቱ ለንግድ ሥራዋ አመቺ የሆነ ስነ-ምህዳር መፍጠሩን ተናግራለች፡፡

የአካባቢው ጽዱና ግልፅ መሆን ያቀረቧቸው አልባሳት እንዲታዩ እና ደንበኞችም በቀላሉ ጎራ ብለው እንዲጎበኟቸው አስተዋፅዖ ማድረጉን ገልፃለች፡፡

በመነፅር ንግድ ሥራ ላይ የምትገኘው ወጣት መክሊት አሰፋ፣ የኮሪደር ልማቱ ለንግድ ሥራ ምቹ መሆኑን በመጥቀስ፣ አካባቢው በፊት ከነበረው በጣም የተሻለ እንዲሆን እንዳስቸለውም ጠቅሳለች፡፡

በዚህም በደንብ እንዲሰሩ እና ከደንበኞችም ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ማስቻሉን ጠቁማለች፡፡

በተለያዩ የመዋቢያ ዕቃዎች ንግድ ላይ የምትሰራው ወጣት የአብሥራ ሞገስ፣ በኮሪደር ልማቱ ባማረው የመንገድ ዳር ሱቅ ውስጥ በግልፅ በሚታዩት ሸቀጦች ሰዎች ተማርከው በመግባት ብዙ ዕቃ እንዲገዙ በማድረግም አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ተናግራለች፡፡

ይህም የኮሪደር ልማቱ በመከናወኑ ገበያቸው እንዲጨምር እና ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻሉንም ነው የጠቀሰችው፡፡

የአካባቢው ንፅህና እና ውበት ሥራ ለመስራት በእጅጉ እንደሚያነሳሳ የገለጸችው ወጣት የአብሥራ፣ ንግድንም በምቾት ለማከናወን እንደሚያግዝ ነው ያነሳችው፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review