የዋጋ ንረት ለመቀነስ በተከናወኑ ስራዎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባችውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል። ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት የዋጋ ንረትን ለመቀነስ በተከናወኑ ስራዎች አመርቂ ውጤቶች ተገኝተዋል። በዚህም የጥቅምት ወር አጠቃላይ የዋጋ ንረት ወደ 11 ነጥብ 7 መቀነሱን ገልጸው፤ ይህም የሪፎርም ስራዎች ከተጀመረ ዝቅተኛው ነው ብለዋል።

ይህም ትልቅ ስኬት በመሆኑ እነዚህ ውጤቶችን ማስቀጠልና ቀሪ ስራዎችን ማከናወን የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋጋጥ ያግዛል ሲሉም ተናግረዋል። የዋጋ ንረቱ ወደ አንድ አሃዝ እንዲቀንስ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት እንደ ኢትዮጵያ ሪፎርም ያደረጉ ሀገራት ትልቁ ፈተና የዋጋ ንረትና ሪፎረም አንድ ላይ ማስኬድ ነው።
በኢትዮጵያ በሚያስደንቅ ሁኔታ የዋጋ ንረትን ባለፉት 20 አመታት በተለይም ከሚሊኒየም ጀምሮ የነበረው የዋጋ ማሻቀብ ረገብ ያለበት ዘመን ነው ያሉት። ይህም የሆነው በግብርና ምርቶች አቅርቦት ሰፊ ስራዎች በመሰራቱና ምርታማነት በመጨመሩ መሆኑን ነው የገለጹት። የገበያ መረጋጋት በዋጋ ብቻ ሳይሆን በምርት አቅርቦትም የታረቀ በመሆኑ ነው ብለዋል።
የገበያ ትስስር በተለይም የሰንበት ገበያዎች አምራችና ምርት ፈላጊን በማገናኘት ማገዙን ተናግረዋል። በአጠቃላይ 440 ቢሊየን ብር ድጎማ ለሴፍትኔት፣ ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅ ለደሞዝ ማሻሻያ መደረጉን አንስተዋል። ይህም ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ከነበረው የአገሪቱ አመታዊ በጀት የበለጠ ነው ብለዋል።
የማእድ ማጋራት፣ የተማሪዎች ምገባ፣ የገንዘብ ፖሊሲና ሌሎች ስራዎችም የኑሮ ውድነትን ለመከላከል እገዛ ማድረጉን አክለዋል።