በእንግሊዝ ካራባኦ ካፕ 4ኛ ዙር ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።
አርሰናል በኤምሬትስ ስታዲየም ብራይተንን ያስተናግዳል። በካራባኦ ካፕ ጥሩ ታሪክ የሌለው አርሰናል ዛሬ ካሸነፈ ሩብ ፍፃሜውን ይቀላቀላል። አርሰናል በካራባኦ ካፕ ለፍፃሜ ከደረሰ ስምንት ዓመታት አልፈዋል። ዋንጫውን ካሸነፈ ደግሞ 32 ዓመት ሞልቶታል።
በሌሎች ጨዋታዎች የውጤት ማጣቱ እየጠነከረ የመጣበት ሊቨርፑል ክሪስታል ፓላስን ያስተናግዳል። ሊቨርፑል በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው ስድስት የመጨረሻ ጨዋታ በአምስቱ ተሸንፏል።
በፕሪሚየር ሊጉም አራት ተከታታይ ጨዋታ ተሸንፈው ከመሪው አርሰናል በሰባት ነጥብ ለመራቅ ተገደዋል። ቀዮቹ ከዚህ አስከፊ ውጤት ለመላቀቅ ከክሪስታል ፓላስ ጋር በአንፊልድ ይጫወታሉ።
ሊቨርፑል በኮሚኒቲ ሺልድ እና በፕሪምየር ሊጉ ፓላስን ገጥሞ በሁለቱም መሸነፉ ይታወሳል። የመርሲሳይዱ ክለብ ካራባኦ ካፕን 10 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚው ክለብ ነው።
ስዋንሲ ሲቲ ከ ማንችስተር ሲቲ ፣ ወልቭስ ከ ቼልሲ እንዲሁም ኒውካስትል ዩናይትድ ከ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ሌሎች ተጠባቂ ጨዋታዎች ናቸው። ኒውካስትል ከ ቶተንሃም ምሽት 5 ሰዓት ሲጀምር ሌሎች ጨዋታዎች በተመሳሳይ ምሽት 4:45 ሲል የሚጀምሩ ይሆናል።
በሸዋንግዛው ግርማ