አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በ2ኛው የውሃ እና ኢነርጂ ሳምንት ላይ ላበረከው የላቀ የሚዲያ ሽፋን እውቅና አገኘ

You are currently viewing አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በ2ኛው የውሃ እና ኢነርጂ ሳምንት ላይ ላበረከው የላቀ የሚዲያ ሽፋን እውቅና አገኘ

AMN-ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአዲስ አባባ ሳይንስ ሙዚየም የተካሄደው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት አውደ ርዕይ ላይ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የልማት አጋሮች፣ የሚዲያ አካላት እና የግል ድርጅቶች እውቅና በመስጠት ተጠናቋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተዘጋጀው 2ኛው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት “ውሃና ንፁህ ኢነርጂ ለዘላቂ ዕድገት” በሚል መሪ ሃሳብ በሳይንስ ሙዚየም በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

አውደርእዩ በሳይንስ፣ በፖሊሲ እና በተግባር መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብና ግልፅ ለማድረግ፤ የምህንድስና እና የውሃ ዲፕሎማሲን ብሎም ስለ ዓለም አቀፍ የውሃ ህግ እና ዲፕሎማሲ ጥልቅ ግንዛቤን ለማዳበር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችን ጉዳይ ኢትዮጵያ ያላት ጽኑና የማይቀር አቋም የቀጠናውን ተገቢ፣ሚዛናዊና ፍትሀዊ የውሃ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለው በነበረው በአራት ቀናት ቆይታም ይሁን በዕለቱ የሚቀርቡ ጽሑፎች፣ፓናል ውይይቶችና አውደ ርዕዮች ዋናው ጉዳይ ተሞክሮዎችንና ልምዶችን በመለዋወጥ በትብብርና በቅንጅት በመስራት የማደግ ጽኑ ፍላጎትን መግለጫ ነው ብለዋል።

በሁነቱ ማገባደጃ መርሃ ግብር ላይ በውሃና ኢነርጂ ሳምንቱ ለተሳተፉና ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ኃላፊነት ለተወጡ የልማት አጋሮች፣ ለግል ድርጅቶች እና የሚዲያ አካላት እውቅና የተሰጠ ሲሆን አዲስ ሚዲያ ኔትወርክም ለነበረው የላቀ የሚዲያ ሽፋን እውቅና ተሰጥቶታል።

በታምሩ ደምሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review