በአተነፋፈስ ስርአት ችግር ከሚከሰቱ ህመሞች መካከል አንዱ ነው አስም፡፡ ይህ ህመም ታዲያ ብዙ ጊዜ ተለዋዋጭነት ባህሪ ያለው መሆኑን የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶክተር ገብረህይወት ለማ ይገልፃሉ፡፡
ሳል፣ ደረትን የማፈን፣ በላይ በላይ መተንፈስ፣ አየር የማጠር እንዲሁም አየር ወደ ውጪ በምናስወጣበት ሰዓት ተጨማሪ ድምፆች መሰማት ብዙ ጊዜ የሚታዩ ምልክቶች መሆናቸውንም ባለሞያው ጠቁመዋል፡፡
ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶክተር ገብረህይወት፣ እናት ወይም አባት፣ የእናት ወይም የአባት ዘመዶች በአስም በሽታ ተጠቂ ከሆኑ፣ ልጆቻቸው ከሌላው ማህበረሰብ አንፃር በአስም የመጠቃት ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን ነው የገለፁት ፡፡
ሌላው ደግሞ በህፃንነት በተደጋጋሚ የአተነፋፈስ ስርአት ወይም የሳንባ ኢንፌክሺን መከሰት ለአስም እንደሚያጋልጥ ነው ያመላከቱት፡፡

በተደጋጋሚ ለተለያዩ ሽታዎች ወይም ለአለርጂ መጋለጥም አስም ሊያመጣ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል በህፃንነት በተደጋጋሚ የቆዳ ላይ ሽፍታ መውጣት እንዲሁም ሳይነስ ያለበት ሰው፣ በህይወት ዘመኑ አስም ሊከሰት የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
አስም እንዲነሳ የሚያደርጉት ነገሮች ብዙ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር ገብረህይወት፣ ቀዳሚዎቹ ኢንፌክሽኖች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
እነዚህም ጉንፋን፣ የሳንባ ምች ወይም ሌሎች የአተነፋፈስ ስርአት አካል ኢንፌክሽኖች በአብዛኛው አስም እንዲነሳ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱም ነው ያመላከቱት፡፡
ሁለተኛው በጣም ቀዝቃዛ እና አቧራማ የአየር ንብረት ሲሆን፣ በዚህም አስም የመነሳት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የምንጠቀማቸው ሽቶዎች፣ በሥራ ቦታችንና በቤታችን ያሉ የተለያዩ ሽታዎች፣ የቤት ቀለማችንን ጨምሮ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ምክንያቶች ለአስም ህመም መነሳት ምክኒያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

የአስም ህመም እንዳይነሳ መሠረታዊ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ተገቢ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ከጥንቃቄዎቹም ውስጥ የአየር ንብረቱ ቀዝቃዛ ከሆነ ታማሚዎች ሻርፕ ወይም ማስክ በመጠቀም ወደ ውስጥ የሚያስገቡት አየር ተገቢውን ሙቀት አግኝቶ እንዲተነፍሱ ቢያደርጉ የህመሙን የመነሳት ዕድል ይቀንሰዋል ነው ያሉት፡፡
ሁለተኛ በመኖሪያ እና በስራ ቦታችን መጥፎ የሆኑ ለታማሚው የማይስማሙ ሽታዎች ካሉ እነዛን ሽታዎች ማስወገድ አስሙ እንዳይነሳ እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
አስም ያለበት ሰውም የሚወስዳቸውን በሃኪም የታዘዙ መድሃኒቶች በአግባቡ መውሰድ እንደሚኖርበት በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
ብዙ ሰዎች አስም ሲነሳባቸው መድሃኒት ቤት ሄደው የሚዋጠውን መድሃኒት በተደጋጋሚ መውሰድ እንደሚታይ የገለጹት ዶክተር ገብረህይወት፣ ይህም ተጓዳኝ በሽታዎች እንደሚያመጣ በመግለፅ መድሃኒት ከመጠቀማቸው በፊት የህክምና ባለሞያ ሊያናግሩ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡
በታምራት ቢሻው