በአሻጥር ያጣነውን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ወቅታዊ፣ ጊዜው የሚያስገድደንና የዜጎች ሁሉ ቀዳሚ አጀንዳ ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ

You are currently viewing በአሻጥር ያጣነውን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ወቅታዊ፣ ጊዜው የሚያስገድደንና የዜጎች ሁሉ ቀዳሚ አጀንዳ ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ

AMN ጥቅምት 25/2018

የባሕር በር ጉዳይ የሕልውናና ሀገርን የማስቀጠል ተቀዳሚ አጀንዳ መሆኑንም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው የመንግሥት አቋምና አቅጣጫዎች ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ጊዜ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ የተደረገበት መንገድ እና ውሳኔ ተፈትሾ ተጨባጭ ማስረጃ መታጣቱን ማንሳታቸው ይታወሳል።

የባሕር በር ጉዳይ የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምሕር ረዳት ፕሮፌሰር ተንሳይ ሐይሉ እንዳሉት፥ በአሻጥር ያጣነው የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ወቅታዊ፣ ጊዜው የሚያስገድደንና የዜጎች ሁሉ ቀዳሚ አጀንዳ ነው ብለዋል።

ሀገራችን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄዋ በታሪክም ሆነ በአለም አቀፍ ህጎች ተቀባይነት ያለው የሕልውና ጥያቄ ነው ያሉት ደግሞ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምሕር አቶ ዋኬና አፍካላ ናቸው።

ይህን ታሪካዊና ሕጋዊ መብቷን በዲፕሎማሲያዊ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ለማግኘት መንግስት የጀመራቸው ተግባራት እና ውሳኔዎች ወሳኝ እርምጃ መሆናቸውን አንስተዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ተንሳይ ሐይሉ አክለው እንደገለፁት፥ ኢትዮጵያ ከባሕር በር የተነጠለችበት መንገድ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አእምሮ ውስጥ የሚመላለስ አሁናዊ የሕልውና ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገርን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ፣ዕድገትና ሕልውና ለማረጋገጥ የመንግስት አቋምና እየተጓዘበት ያለው መንገድ ትክክለኛና ወቅታዊ ነው ብለዋል።

ከ130 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እና ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት አገር ባሕር ተዘግቶባት ሕልውናዋን ማስቀጠል አይቻልም የሚሉት ደግሞ መምሕርና የአፍሪካ ቀንድ ፀሐፊ አቶ ዋኬና አፍካላ ናቸው።

የባሕር በር ጥያቄን በአለምአቀፍ ሕጎችና በጋራ የመልማት ተቀዳሚ ዲፕሎማሲያዊ መርሕ ከዳር ለማድረስ የተቀናጀ ጥረቱ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ተንሳይ፥ የሕልውና ጥያቄ የሆነውን የባሕር በር የማግኘት ጉዞ በማሳካት ረገድ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ጭምር ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።

በተለይም የኢትዮጵያን መልማትና ማደግ ባገኙት አጋጣሚ የሚያጠለሹት ግብፅን የመሳሰሉ ታሪካዊ ባላንጣ ሀገራትን መልዕክቶች በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ በማጋለጥ የሀገራችንን በጋራ የመልማት ተቀዳሚ መርሕን ማሳወቅ ላይ መረባረብ ይገባናል ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review