ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደውን የሴራ ፖለቲካ በመቀየር የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ማተኮር እንደሚጠበቅባት የቀድሞ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ኢብሳ ነገዎ ገለጹ፡፡
አቶ ኢብሳ ነገዎ በአንድ ወቅት የቀድሞውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግን) ተቀላቅለው ኤርትራ በነበሩበት ወቅት በቅርበት የታዘቡትን ለኤኤምኤን እንደገለጹት የግብፆች የሁልጊዜ ተግባር ኢትዮጵያን ማፍረስ እና እርስ በእርስ ማገዳደል ነዉ፡፡
በጊዜው ከግብጽ ገንዘብ እንደሚመጣ እና እኩይ ሥራቸው እንዳይታወቅ በሦስተኛ ወይም በአራተኛ ወገን እንደሚታደል የሚናገሩት አቶ ኢብሳ፣ በኤርትራ በኩል የገንዘብ ማስተላለፍ ድለላ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

እርስ በእርስ ጥርጣሬ እንዲነግስ ማድረግ፣ ሀገር እንድትተራመስ ከዚህም ሲያልፍ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረግ ትጋት የግብጾች አላማ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖው እንዳለ ሆኖ በሃይማኖት በኩልም በማይታዩ እጆች ተፅዕኖ ለማድረስ ሲካሄድ የቆየ እንቅስቃሴ መኖሩን በመጠቆም ኢትዮጵያ ወደ ኋላ እንድትቀር የማድረግ ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር እንደሚያደርጉ የተናገሩት አቶ ኢብሳ በነፃነት ሥም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠሩ ማናቸውም የፖለቲካ ድርጅቶች በግብፅ አማካኝነት መፈጠራቸውን ተናግረዋል፡፡
ግብጾች ለኤርትራ በስልጠና፣ በዲፕሎማሲ እና በመሳሪያ ደረጃ እርዳታ እንደሚሰጡም አመላክተዋል፡፡
ይህንንም የሚያደርጉት በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዳይኖር ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በታምራት ቢሻው