ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን የልማት አጋርነት በኢንዱስትሪ ዘርፍም አጠናክራ ትቀጥላለች

You are currently viewing ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን የልማት አጋርነት በኢንዱስትሪ ዘርፍም አጠናክራ ትቀጥላለች

AMN ጥቅምት 27/2018

ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የተመሰረተውን የልማት አጋርነት በኢንዱስትሪ ዘርፍም አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋገጠች።

‘’ቻይና ለአፍሪካ ኢንዱስትሪ፣ ለአረንጓዴና ዘላቂ ልማት ድጋፍ ታደርጋለች’’ በሚል መሪ ሀሳብ በቻይና የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ እና የውይይት የጥናትና ትብብር ማዕከል ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ (POA) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መድረክ እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ የቻይና የሥራ ኃላፊዎች የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የተለያዩ ዘርፎች ኮሚሽነሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

በቻይና የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ሃላፊና በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካይ አምባሳደር ጂያንግ ፌንግ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የአፍሪካ ኢንዱስትሪ አረንጓዴ የተቀናጀና ዘላቂ ልማትን የሚያበረታታ በመሆኑ ቻይና ድጋፏን ታጠናክራለች።

የኢንዱስትሪ መስፋፋት ለአፍሪካ ቀጣይነት ያለው ልማትና ዕድገት ወሳኝ መሆኑንም ነው ያነሱት።

የአፍሪካ የ2063 አጀንዳ እውን እንዲሆን ኢንዱስትሪውን ማስፋት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት በልማት እቅዳቸው የኢንዱስትሪን ጉዳይ ትኩረት መስጠታቸውን አድንቀዋል።

ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የተመሰረተ አጋርነት በኢንዱስትሪ ዘርፍም አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ቻይና የአፍሪካ ሀገራትን በመንገድ መሰረተ ልማት በማስተሳሰር ለኢንዱስትሪ ዕድገቱ ጉልህ ሚና እየተጫወተች መሆኑንም አንስተዋል።

የቻይና ባለሀብቶች በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በኢንዱስትሪ ማስፋፋት፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታና በሌሎችም ዘርፎች መሰማራታቸው የልማት አጋርነቷን የሚያሳይ መሆኑን ነው ያነሱት።

በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር ሌራቶ ዶሮቲ በበኩላቸው፤ አፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቷን በመጠቀም ልማቷን ለማረጋገጥ እየሰራች ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ልማት የሚያድገው ኢንዱስትሪን በማስፋፋት፣ የሰው ሃይሉን በአግባቡ መጠቀም ሲቻል መሆኑንም አንስተዋል።

ቻይና በአፍሪካ ዲጂታላይዜሽንና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት እንዲሁም የሰው ሃይል በማሰልጠን እያደረገችው ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

የአፍሪካ ህብረት ከቻይና ጋር የዲጂታል ኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ልማት በማስፋፋት ለአጀንዳ 2063 እውን መሆን በጋራ ይሰራል ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አማካሪ ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪን ልማት ዋነኛ የልማት አጀንዳ አድርጋ እየሰራች ነው ብለዋል።

በርካታ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ መዕዋለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በጋራ የመልማት ፍላጎትን ያሳያል ብለዋል።

ዘላቂና አስተማማኝ ልማትን ለማረጋገጥ ኢንዱስትሪ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማቷን ለማረጋገጥ ከሀገራት ጋር በጋራ ትሰራለች ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review