የጥበባዊ ማዕከላቱ ሌላኛው ገጽ

You are currently viewing የጥበባዊ ማዕከላቱ ሌላኛው ገጽ

ዛህራ አል-ዛድጃሊ የኪነ ጥበብ ሥራዎችና የጥበብ መድረኮች ከባህል እሴቶች ጋር ያላቸውን ተዛምዶ ያጠኑ ምሁር ናቸው፡፡ “The Significance of Art in Revealing a Culture’s Identity and Multiculturalism” በሚል ርዕስ በፈረንጆቹ በጥር 2024 ያሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ ይህንኑ ጭብጥ በስፋት ይዳስሳል፡፡ በዚህ ጥናት ላይ እንደሰፈረው፣ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎችና ክዋኔዎች የባህልን ማንነት አጉልቶ በማሳያነትና በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ ከእነዚህ ሚናዎች መካከል የህብረተሰቡን አተያይ በመቅረጽ፣ የጋራ ማንነትን በመፍጠርና ማኅበራዊ ትስስርን በማጎልበት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው የሚለው አንዱ ነው፡፡ በተለይ የክውን ጥበባት በጋራ የሚደረጉ ልምምዶች በመሆናቸው ህብረትንና የጋራ ርዕይን የመቅረጽ አቅም አላቸው። ምክንያቱም ሰዎች በአንድነት ሆነው ትርዒት ሲመለከቱና በትርዒቱ ሲሳተፉ የጋራ ስሜታዊ ተሞክሮ ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የኅብረተሰብ ስሜትን፣ አብሮነትን እና የጋራ ማንነትን እንደሚያጠናክር ምሁሯ በጥናታቸው አስፍረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ ጥንታዊ ስልጣኔና ረዥም የመንግስትነት ታሪክ ካላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ ከዚህ ጥንታዊ ሥልጣኔና ታሪክ የወረስናቸው መልከ-ብዙ ቅርሰ-ውርሶች (legacies) ደግሞ ኢትዮጵያን አድምቀዋታል። እነዚህን ቅርሰ-ውርሶች ኢትዮጵያን ባለ-ብዙ ባህል፣ ሀይማኖት፣ ቋንቋ፣ ሙዚቃ፣ ጭፈራ… ባለቤት እንድትሆንም አስችሏታል፡፡ ዛሬ ላይ የምናያቸው መልከ ብዙ ትውን ጥበባትና ክዋኔዎች የታሪካችን ቅርሰ-ውርሶች ናቸው፡፡

በተለይ እንደ ጭፈራና ሙዚቃ ያሉ ጥበባዊ ክዋኔዎች የማህበረሰቡ አካል ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ጭፈራ፣ በክዋኔ የታጀቡ የወል ዘፈኖችና የሙዚቃ መሳሪያዎችን መጫወት የባህል ልምምድ እንጂ ትምህርት ቤት ውስጥ ገብተው የሚማሩት ነገር አይደለም፡፡ እነዚህ ክዋኔ ጥበባት የማህበረሰቡ አካል በመሆን አባላቱን ለዘመናት ያስተሳሰሩ እሴቶች ናቸው፡፡ በዚህ አጭር ዓምድም በመዲናችን አዲስ አበባ የተገነቡ ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ማዕከላት ትውን ጥበባትና ልዩ ልዩ ማህበረሰባዊ የጥበብ ክዋኔዎች ይበልጥ ጎልተው እንዲወጡ፣ እንዲያድጉና የአስተሳሳሪነት ሚናቸው እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ ያላቸው ሚና ምን እንደሚመስል በጨረፍታ ዳስሰናል፡፡

ባህል፣ እሴት፣ ጥበባዊ ክዋኔዎች እና ጥበባዊ መድረኮች

ኢትዮጵያ ብዝሃ ማህበረሰብና ባህሎች ያሉባት ሀገር ነች፡፡ በዚሁ ልክ መልከ-ብዙ ጭፈራዎች፣ ባህላዊ ሙዚቃዎችና ክውን ጥበባት ያሏት ሀገር ነች፡፡ ለአብነትም የሙዚቃ ዝግጅት ከሚደረግባቸው የባህል ምሽቶች ውስጥ የሀገራችን መልከ-ብዙ ጭፈራዎችና በክዋኔዎች የታጀቡ የባህል ሙዚቃዎች መመልከት ብዙም እንግዳ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያንም በእነዚህ ክዋኔዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ሲዝናኑ መመልከት የተለመደ ነው። ነገር ግን ተሳትፎው ከመዝናናት ወይም በክዋኔዎቹ ከመታደም የተሻገረ ጥልቅ አስተሳሳሪ የወል ማንነትን እንደሚፈጥሩ የባህል (ፎክለር) እና ኪነ ጥበባዊ ጉዳዮች ተመራማሪ ወሰን ባዩ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት አብራርተዋል፡፡ ክውን ጥበባት መድረክ ላይ በሚቀርቡበት የጥበብ መድረክ ላይ ስንታደም ከሌሎች ባህሎች፣ ልምዶች እና ታሪኮች መማር ብቻ ሳይሆን ዕሴትንም የመጋራት ዕድል ይፈጥርልናል፡፡ በዚህ ምክንያት በተለያዩ ባህሎች እና አመለካከቶች መካከል የእሴቶች መወራረስና የጋራ ማንነት እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሚና ብዙሃኑን ከማዝናናት ባሻገር ስለ ራሳችን በጥልቀት እንድናውቅ፣ በልዩነት ውስጥ የጋራ ማንነት እንዳለን እንድንገነዘብና በሀገራዊ ጉዳይ ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንድናደርግ ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ምሁሩ አጫውተውናል፡፡

እነዚህ መልከ-ብዙ ክውን ጥበባት ትልቅ የሆነ አስተሳሳሪ ሚና እና ማንነታችንን ይበልጥ እንድንገነዘብ የሚያስችሉን እሴቶች በመሆናቸው፣ ዘመኑን የዋጁ መድረኮች ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ የባህሎችና እሴቶች መወራረስ እንዲፈጠር የሚያደርጉትም ዜጎች የሚሰባሰቡባቸው ምቹ መድረኮች ሲኖሩ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በመዲናዋ የተገነቡ ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ማዕከላት እነዚህን እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ በማስቻል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመዲናችን አዲስ አበባ ነባር የቴአትር ቤቶችን በዘመናዊ መልክ ከማደስ ጎን ለጎን አዳዲስ ዘመናዊ ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ማዕከላት ተገንብተው ተመርቀዋል፡፡ ለአብነትም በቅርቡ እንኳን የህፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስን ጨምሮ፤ እጅግ ዘመናዊ እንደሆኑ የተመሰከረላቸው አዳዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ህንፃዎች ተመርቀዋል፡፡  

የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከሳምንት በፊት የተመረቀው የአዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ህንፃን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መረጃ፣ አዲሱ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ህንፃ፣  ባለ 15 ወለል ነው። የህንፃው አጠቃላይ ስፋት 24 ሺህ ካ.ሜ ሆኖ  ባለ አራት ወለል የመኪና ማቆሚያ የያዘ ነው። 592 ህፃናትንና 887 አዋቂዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው ሁለት የሲኒማ አዳራሾችን ጨምሮ  በቂ የሆነ የድምፅ ማስተላለፊያ ሲስተም፣ ዘመናዊ የመብራት ስርጭት፣  የአየር መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን አካትቷል። በተጨማሪም፤ ለቢሮዎች፣ ለስቱዲዮ፣ ለሥዕል እና አርት ጋለሪ፣ ለቤተ መጻሕፍት እና ለተለያዩ ተያያዥ አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎችን ማሟላቱን ባጋሩት መረጃ ይፋ አድርገዋል፡፡

በመዲናዋ የተገነቡ እነዚህ ዘመናዊ ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ማዕከላት ትልቁ ዓላማቸው ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች እንዲጎለብቱ ማገዝ ነው፡፡ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ ከማህበረሰቡ ባህልና እሴት የሚመነጩ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት የአንድ ሀገር ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች ማደግ በማህበረሰቡ ውስጥ መልከ-ብዙ አስተዋጽኦ እንዳለው ጥናቶች ያሳያሉ። በመዲናዋ የተገነቡ ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ማዕከላት በዜጎች ላይ የሚፈጥሩት አዎንታዊ ተጽዕኖ ትውልድን ከማነጽ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ትውልዱ ከማንነቱ ጋር ይበልጥ እንዲተዋወቅ፣ እሴቶቹን እንዲያከብርና ለቀጣይ ትውልድ እንዲያስተላልፍ መደላድል ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ትውን ጥበባትና ክዋኔዎች መድረክ እንዲገኙና ይበልጥ እንዲጎለብቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

መሐመድ አልዶጋን የተባሉ ተመራማሪ፣ በፈረንጆቹ በሰኔ 2025 በሪሰርች ጌት ገጸ-ድር ላይ “Performing Arts and Audience Satisfaction” በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ ክውን ጥበባት ምቹ መድረክ አግኝተው ለሕዝቡ ሲቀርቡ ህብረተሰቡን ከማዝናናት ያለፈ ሚና እንዳላቸው አስፍረዋል፡፡ ክውን ጥበባት ማህበረሰባዊ እሴቶችን አጉልቶ ማሳየት ብቻም ሳይሆን በክውን ጥበባት አማካኝነት ማህበረሰቡን የመሄስ አቅም አላቸው። ማህበረሰቡ ራሱን እንዲመለከት ያደርጋሉ፡፡ ተመልካቾችም የተለያዩ አመለካከቶችን እንዲያዳምጡና መልከ-ብዙ እሴቶችን እንዲያውቁ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ። እነዚህን ጥበባዊ ተግባራት ዕውን ለማድረግ የጥበብ ማዕከላትና መድረኮች ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት የመዲናዋ አዳዲስ ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ማዕከላት ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡

ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎችና ክውን ጥበባት የማህበረሰቡ እሴቶች መሆናቸውን ያጫወተን ደራሲና ሃያሲ ዋለልኝ አየለ፣ እነዚህን ጥበባዊ እሴቶች ጠብቆ ለማቆየትና ይበልጥ እንዲጎለብቱ አመቺ ሁኔታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በከተማዋ የተገነቡ ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ማዕከላት በዚህ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ እነዚህ ዘመናዊ ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ማዕከላት ባህልን ያሳድጋሉ፤ እሴቶችን ጠብቀው ለትውልድ ለማቆየትም ቁልፍ ሚና አላቸው። በተለይ ብዙም ትኩረት ያላገኙና በተለያዩ ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ ክውን ጥበባት ይበልጥ መድረክ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ ብሎ እንደሚጠብቅ አጫውቶናል፡፡

የሀገራት ተሞክሮን ስንመለከት ምቹ የጥበብ ሥፍራዎችና በስፍራዎቹ ላይ የሚከይኑ ኹነኛ ባለሙያዎች መኖር ለአንድ ሀገር ሃያልነት ትልቅ ሚና እንዳለው መረዳት አይከብድም፡፡  ለዚህ ጥሩ አብነት አሜሪካ ነች፡፡ ዛሬ ላይ አሜሪካ ልዕለ ሃያል ሀገር እንድትሆንና ተጽዕኖዋ መላው ዓለም እንዲዳረስ ካደረጉ ተቋማት መካከል ዋነኞቹ የባህልና የጥበብ ተቋሞቿ እንደሆኑ ይታወቃል። ለዚህ ጥሩ ማሳያው ሆሊውድ ነው፡፡ ሆሊውድ ከ1920ዎቹ ጀምሮ የአሜሪካ የፊልም ኢንዱስትሪ (Cinema) እና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ዋና ማዕከል በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ስም ነው። “ሆሊውድ” የሚለው ስም ራሱ በብዙ መልኩ የአሜሪካን የፊልም እና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ በጠቅላላ የሚወክል ሆኗል። ይህ ኢንዱስትሪ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚንቀሳቀስበት ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ተመልካችን ለመሳብ የተበጁ ዘመናዊ እና ግዙፍ ፊልሞችን በማምረት ይታወቃል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ከሆሊውድ ጋር ያለው ትስስር ጥልቅ እና ውስብስብ ነው። ሆሊውድ ለአሜሪካ “ለስላሳ ኃይል” (Soft Power) ከሚባሉት ዋና መሳሪያዎች መካከል አንዱ ነው። ከዚህ አንጻር አሜሪካ የባህል ማስፋፋት (Cultural Diffusion) የምትከውንበት ዋነኛ መሳሪያዋ ነው። ሆሊውድ በአሜሪካ የአኗኗር ዘይቤ፣ ልማድ፣ እሴቶች እና ፋሽን ወደ ሌላ ዓለም በማሰራጨት ረገድ ትልቅ ተጽዕኖ አለው። ፊልሞች እና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የአሜሪካን ባህልና የአስተሳሰብ ዘይቤ ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሰፊው ያሰራጫሉ፡፡ ይህም የአሜሪካን ምርቶች እና አገልግሎቶች ተቀባይነት እንዲያገኙ ያግዛል። ምንም እንኳን የመዝናኛ ዓላማ ቢኖራቸውም፣ የሆሊውድ ፊልሞች ብዙውን ጊዜ የአሜሪካን የፖለቲካ አስተሳሰቦች፣ ጀግንነት እና ልዕለ-ሃያልነትን ያንፀባርቃሉ። እነዚህ መልዕክቶች በዓለም አቀፍ ተመልካቾች ዘንድ ስለ አሜሪካ አዎንታዊ ግንዛቤ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። መዘንጋት የሌለበት አንዱ ቁልፍ ጉዳይ ግን የዚህ ሁሉ ምንጭ አሜሪካ የገነባችው እጅግ ዘመናዊ የፊልም ማምረቻ መንደርና ለዚህ ግዙፍ የሲኒማ መንደር የሰጠችው ትኩረት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የተገነቡ ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ማዕከላት የማህበረሰቡን የክውን ጥበባት እሴቶችን ከመጠበቅ ባሻገር፣ የአፍሪካ መዲና ለሆነችው አዲስ አበባም ሆነ ኢትዮጵያ ተጽዕኖዋ ይበልጥ እንዲጎላም ያስችላሉ፡፡

በአጠቃላይ በመዲናዋ የተገነቡ የጥበብ ማዕከላትና ዘመናዊ ቴአትር ቤቶች ትውልድን በማነጽና ነባር እሴቶችን ወደ ቀጣዩ ትውልድ በማሻገር ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡ የፈጠራ ስራዎች እንዲዳብሩ፣ እንደ ክውን ጥበባት ያሉ ባህላዊ እሴቶች መድረክ እንዲያገኙና የወል ማንነት እንዲገነባ ምቹ መደላድል ይፈጥራሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የመዲናዋ አዳዲስ ቴአትር ቤቶችና የጥበብ ማዕከላት ዘመን ተሻጋሪ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review