በአንድ ጀምበር ብቻ ለ2 ሺህ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች የስራ ዕድል መፍጠሩን የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ባለፉት 6 ወራት ለ2ሺ የክፍለ ከተማው ስራ ፈላጊዎች የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን ሲሰጥ የቆየው የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አስተዳደር፤ ስራ ፈላጊዎችን ከተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር በማስተሳሰር የስራ ባለቤት እንዲሆኑ አስችሏል፡፡
በለሚ ኩራ ከፍለ ከተማ በ 2018 በጀት ዓመት ከ 37 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚና የስራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ልመንህ ምህረቱ ተናግረዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ ብቻ ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን የገለጹት አቶ ልመንህ፤ በአንድ ጀምበር ብቻ ለ2 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯልም ነው ያሉት፡፡
ኢንዱስትሪዎች እና ድርጅቶች ለስራ ዕድል ፈጠራ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ደቻሳ አሳስበዋል፡፡
በአንድ ጀምበር ብቻ 2 ሺህ ባለሙያዎችን ከቀጣሪዎች ጋር ለማስተሳሰር በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ወጣቶችም ያገኙትን ዕድል በመጠቀም እራሳቸውን እና ሀገራቸዉን መለወጥ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ይህ እድል ለበርካታ ጊዜ ሲናፍቁት የነበረ አጋጣሚ ስለመሆኑ የሚናገሩት የስራ ዕድል ተጠቃሚ የክፍለ ከተማው ወጣቶች ያገኙትን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ የሙያ መስኮች ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎችን ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ የቀጣሪ ድርጅት ባለቤቶች ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች እና ሴቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡
በቴዎድሮስ ይሳ