ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ ለማዘጋጀት እጩ ሆና ቀርባለች፡፡
ከ2 ዓመት በኋላ እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ስሌት በ2027 ለሚካሄደው 32ኛው የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) ኢትዮጵያ አስተናጋጅ ሆና በእጩነት መመረጧን የዘንድሮው የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (COP30) ፕሬዝዳንት ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የCOP30 ተሳታፊ ሀገራት 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ለማካሄድ በመርህ ደረጃ መስማማታቸውን ነው ፕሬዝዳንት አንድሬ ኮርያ ዶ ላጎ ያስታወቁት፡፡
ይሁን እንጂ ምርጫው በመደበኛነት ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል ያሉት ፕሬዝደንቱ ይሄም ዛሬ ማክሰኞ ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል፡፡
በመስከረም ወር ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የ2027ቱን ጉባኤ ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው ኢትዮጵያ የተመረጠችው፡፡
ለቀጣዩ አመት COP31 አስተናጋጅ ሃገር ምርጫ አሁንም አከራካሪ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ አውስትራሊያ እና ቱርክ ቀጣዩን ጉባኤ ለማዘጋጀት እየተወዳደሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
በካሳሁን አንዱአለም