በአዲስ አበባ ከተማ የተሰራው የኮሪድር ልማት በግንባታ ወቅትም ሆነ ግንባታዉ ከተጠናቀቀ በኋላም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡
አቶ ለገሰ በቀለ ለአመታት የስራ እድል በማጣት ሲቸገሩ ነበር ይገልጻሉ፡፡ አሁን ላይ ግን በከተማዋ በተከናወነው የኮሪደር ልማት ሥራ የካሜራ ባለሞያ በመሆን የስራ እድል እንደተፈጠረላቸዉ ተናረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸላዉ የብድር አገልግሎት የፎቶ ካሜራ ገዝተዉ ስራ መጀመራቸዉን የገለጹት አቶ ለገሰ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ብድራቸውን ከፍለው መጨረሳቸዉን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ቀን ከሌሊት በአዲስ አበባ ከተማ በተሰሩ አራቱም የኮሪደር ልማት ስፍራዎች በመዘዋወር ፎቶ በማንሳት የተሻለ ገቢ በማግኘት ላይ መሆናቸዉን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ለገሰ የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ተቺዎች እንደሚሉት መብራት እና ብልጭልጭ ነገር ብቻ ሳይሆን፣ ሰው ተኮር የልማት ስራ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የስራ እድል የተፈጠረላቸው የካሜራ ባለሞያዎች በቂ ማሳያዎች ናቸው ሲሉ ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል።
አቶ ለገሰ እና ሌሎች የካሜራ ባለሞያዎች በማህበር ተደራጅተው በአድዋ ድል መታሰቢያ፣ በእንጦጦ ፓርክ፣ በአራት ኪሎ ፕላዛ እና በካዛንቺስ አካባቢ በፎቶ ማንሳት ስራ ቤተሰቦቻቸውን እያኖሩ እና ኑሮአቸውንም እየቀየሩ ይገኛሉ።
ፒያሳ ዉስጥ ከአሁን ቀደም ለደቂቃዎች መዝናናትም ሆነ ፎቶና ቪዲዮ መነሳት የሚታሰብ አይደለም፡፡ መጥፎ ሽታዉ ለአፍንጫ ፤ አካባቢዉም ለአይን አይመችም ነበር፡፡
አሁን ላይ ግን ቦታ በመልማቱ፣ መሄጃና መናፈሻ አጥተው የነበሩ በእድሜ የገፉ አዛውንቶች፣ በእነዚህ የለሙ ስፍራዎች ላይ ቁጭ ብለው ማውጋት መቻላቸዉን፤ ለወጣቶችም የስራ እድል መፈጠሩን አቶ ለገሰ ጠቁመዋል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ