በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ በፍጥነትና በጥራት በ24 ህንፃዎች የተገነቡትን 1,287 ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች በይፋ መመረቃቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
የሁላችን መዲና የሆችው ከተማችንን የማርጀት እና የመቆሸሽ ታሪክ በየዕለቱ እየቀየርን፤ የማህበረሰባችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ በርካታ ውጤታማ ስራዎችን እያከናወን ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተለይም የሕዝባችንን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከ 380,000 (ሶስት መቶ ሰማንያ ሺህ) በላይ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል ብለዋል።
ይህም ከለውጡ በፊት ባሉት 17 ዓመታት ከተገነቡት 179,000 (መቶ ሰባ ዘጠኝ ሺህ) ቤቶች እጅጉን የላቀ ነው።
የመፍጠርና የመፍጠን መርህን በተጨባጭ ካረጋገጥንባቸው ፕሮጀክቶች ይህ ትልቅ ስኬት 24/7 የሥራ ባህልን በተግባር ላይ በማዋል የተገኘ ዉጤት መካከል አንዱ ነው።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በጀርመን አደባባይ፣ በአየር ጤና እና በግራር አካባቢ የሚገኙ ናቸው።
ዛሬ የተመረቁት ከ11 እስከ 18 ወለል ያላቸው 24 ሕንፃዎች የያዙት የመኖሪያ ቤቶችን ብቻ ሳይሆን ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ጭምር ነው።
ይህም የልጆች መጫወቻ ስፍራዎችን፣ የስፖርት ሜዳን፣ የመዝናኛ ስፍራዎችን ፣ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን እና ሌሎች የጋራ መገልገያዎችን አሟልተዋል ።
ይህ ፕሮጀክት ከግንባታ ባለፈ በርካታ የሥራ ዕድሎችን እና የእውቀት ሽግግርን ለወጣቶቻችን አስገኝቷል፤ የግንባታ አቅም ፈጥሯል፤ በተጨማሪም ጥራትንና ፍጥነትን በተመሳሳይ ጊዜ ማረጋገጥ እንደምንችል አሳይቷል። ቤቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ለንግድ ባንክ ሰራተኞች ያስረከብን በመሆኑ በአንድ በኩል የቤት እጥረትን ለመፍታት አማራጭ እርምጃ ያስቀመጠ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የቤት ልማት ፈንድን የፈጠረ ጭምር ነው።
ከንቲባ አዳነች ለዚህ ሥራ ስኬት የበኩላቸውን የተወጡ አመራሮችን፣ ባለሙያዎችን እና ተቋማትን በራሳቸውና በከተማ አስተዳደሩ ስም አመስግነዋል።