የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግ በኢትዮጵያ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ባደረግሁት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ላደረጉልን ሞቅ ያለ አቀባበል እናመሰግናለን ብለዋል።
ትብብርን በማጠናከር እና ለንግድ ስራዎች አዳዲስ በሮችን በመክፈት ረገድ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
እንዲሁም የክህሎት ልማት እና የካርቦን ክሬዲቶች ልውውጥን ተመልክተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ፍላጎቶቻችን የሚስማሙባቸው ቁልፍ ዘርፎች ናቸው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሲንጋፖር አዲስ ኤምባሲ በአዲስ አበባ ለመክፈት የወሰደችውን ውሳኔ በደስታ መቀበላቸውንም አመልክተዋል።
ውሳኔው ትልቅ ምዕራፍ እንደሚሆን በማንሳትም፣ ይህም ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ ህብረት እና ከሰፊው አህጉር ጋር ወሳኝ ትስስር ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
ሲንጋፖር እና ኢትዮጵያ ወደ ወሳኝ ቀጣናዎቻችን የሚወስዱ በሮች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሽርክናችንን በማጠናከር፣ ለቀጣዮቹ ዓመታት ሕዝቦቻችንን የሚጠቅም በደቡብ ምስራቅ እስያ እና በአፍሪካ መካከል ድልድይ እየገነባን ነው በማለትም አክለዋል።
በታምራት ቢሻው