AMN ህዳር 18/2018 ዓ.ም
አንዳንድ አሽከርካሪዎች በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚፈጽሙትን እንግልት ለመቅረፍ ብዝሃ ትራንስፖርት በማስፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የትራንስፖርት አገልግሎት ክትትል እና ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ታመነ እንደገለጹት ቢሮዉ አሁኑ ጊዜ በከተማዋ 15ሺህ547 ተሽከርካሪዎችን በማሰማራት የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ አሽከርካሪዎች የግል ጥቅም ለማግኘት ሲሉ መስመር በማቆራረጥ ፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈል ፣ ከተፈቀደው በላይ በመጫን እንዲሁም ተሳፋሪዎችን በማጉላላት የቅሬታ ምንጭ በመሆን ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ቢሮዉ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን ነድፎ እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሃላፊዉ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም 25 እና ከዚያ በላይ ሰዎችን የመጫን አቅም ያላቸው አዉቶቡስ ተሽከርካሪዎችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህንን የመፍትሄ አማራጭ ተግባራዊ ለማድረግ መንግስትና የግል ባለሀብቶች በአጋርነት የሚሰሩበትን ሂደት ተግባራዊ ለማድረግ መታሰቡንም ጠቁመዋል።
በመዲናዋ የህዝብ ትራንስፖርት ከሚሰጡ ሚኒ ፣ ሚዲ ባስ እና ብዝሃ ትራንስፖርቶች መካከል በተለይ ሚኒ ባስ ታክሲዎች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የሚፈጽሙትን የደንብ ጥሰት ለመግታት በተርሚናሎች ላይ የቁጥጥር እና የክትትል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ቢሮው ካስቀመጠው የስምሪት አቅጣጫ ውጭ ወይም ታፔላ ሳይኖራቸዉ ውስጥ ለውስጥ እና በዋናው መንገድ የሚሰሩ አሽከርካሪዎች መሆራቸዉን ያነሱት ሃላፊዉ ችግሩን በህግ አግባብ ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን ፣ አገልግሎቱ በሚሰጥባቸው 94 የምሽት መስመሮች ቅጥቅጦችን ፤ ሀይገሮችን እና አውቶቡሶችን ታሳቢ ያደረገ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሠጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሔለን ተስፋዬ