ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ የአቪዬሽን ጉዞ ውስጥ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
በሞሮኮ ራባት በተካሄደው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ በቢሾፍቱ ስለሚገነባው ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የፋይናንስ፣ የቴክኒካል እና ስልታዊ መሰረት ላይ ዝርዝር ገለጻ ተደርጓል።
በዚሁ ወቅት ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እንደገለጹት፤ በፎረሙ ላይ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች፣ ልማታዊ የፋይናንስ ተቋማት፣ የኤክስፖርት ብድር ኤጀንሲዎችና የንግድ አበዳሪዎች በተገኙበት የፕሮጀክቱን የፋይናንስል፣ ቴክኒካል እና ስልታዊ መሠረቶች ዝርዝር ገለጻ መደረጉ ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ የአቪዬሽን ጉዞ ውስጥ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን አስገንዝበው፤ በዘመናዊው ቴክኖሎጂ፣ በዲዛይን ብሎም ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከል ያደርጋታል ብለዋል።
ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ አኅጉሪቱን ከዓለም ጋር የሚያገናኝ ቁልፍ መግቢያ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ይህ ፕሮጀክት ከአውሮፕላን ማረፊያ በላይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በመላው አፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም እንዲሁም ለቀጣናዊ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትስስር የለውጥ አንቀሳቃሽ ተደርጎ እንደሚወሰድም አስረድተዋል።
በቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ እየጨመረ የመጣውን ጫና እንደሚያቃልልና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም አመላክተዋል።
በአጠቃላይ የዐቅም ውስንነቶችን በማስወገድ ኢትዮጵያ ብሎም መላው አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲገናኙ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።
ተቋማዊ ባለሀብቶች፣ የንግድ አበዳሪዎች እና የኤክስፖርት ብድር ኤጀንሲዎች በፕሮጀክቱ ላይ እንዲሳተፉ፣ የኢንቨስትመንት ፓኬጁን እንዲገመግሙና በአፍሪካ እጅግ በጣም ትልቅ ከሆኑት የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አንዱ ለመሆን ለተዘጋጀው ሥራ አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል።
በፎረሙ የተሳተፉ የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ በተቋማዊ ባለሀብቶች ዘንድ ለፕሮጀክቱ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸው ተገልጿል።
ይህም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ አኅጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ማዕከል የመሆን ዐቅምን አጉልቶ እንደሚያሳይ የገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘዉ መረጃ አመላክቷል።
አውሮፕላን ማረፊያው ከሕዝብ ትራንስፖርት በተጨማሪ ከፍተኛ መጠን ያለው የጭነት ማጓጓዝ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተጠቁሟል።