ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች አካል መሆን እንዳለባት የፈረንሣይ የምድር ኃይል አዛዥ ጄነራል ፒየር ሺል ገለፁ።
ከቀናት በፊት በሁለትዮሽ ወታደራዊ ጉዳዮች ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጄነራል መኮንኖች ጋር የመከሩት ጄነራል ፒየር ሺል የተለያዩ ተቋማትን ከጎበኙ በኋላ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋርም ተወያይተዋል።
“ኢትዮጵያ የባህር በር በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት ያላትን ፍላጎት እንዴት ይመለከታሉ?” በሚል ከመከላከያ ሚዲያ ጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የፈረንሣይ የምድር ኃይል አዛዥ ጄነራል ፒየር ሺል፤ “ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ ሐገር ናት፣ በጣም ትልቅ የኢኮኖሚ ኃይልና ሕዝብም ያላት በመሆኑ የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች አካል መሆን አለባት ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር የተካሄደው ወታደራዊ ትብብር ዋነኛ ዓላማም ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማሻሻል አዲስ አበባ በመገኘቴ በጣም ኮርቻለሁ ብለዋል።
ስለዚህ ትብብራችን በዋናነት የወታደራዊ ቁሳቁስ ድጋፍ ፣የሠላም ማስከበር ሥራዎች፣ የፈንጅ አወጋገድ ተግባራት ላይ፣ በሠው ኃይል ሥልጠና እና በሌሎችም ነው” ብለዋል።
ጄነራል ፒየር ሺል ኢትዮጵያ የቀጠናውን ደኅንነት ለማስጠበቅ ዋነኛ ተዋናይ መሆኗን ገልፀው፣ የኢትዮጵያ ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንና እንደ ፈረንሣይ ሠራዊት ተወካይ የኢትዮጵያን ሠራዊት እንደሚደግፉም አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ሠራዊት ተሣትፎ በማድነቅ “ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ ሐገር ናት፣ በጣም ጠንካራና ትልቅ ሠራዊትም አላት ከዚህ ሠራዊት ብዙ የምንማረው ነገር አለ ሲሉም አስረግጠው መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኤ ኤም ኤን የላከው መረጃ ያመለክታል።
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዋናው መምሪያ የዓለም ኃያላንን ጨምሮ የተለያዩ ሐገራት የጦር መሪዎችን አስተናግዷል።