አሁን ላይ በመዝናኛ እና በስራ ቦታዎች፤ በጉዞ ላይ፤ በስብሰባና በተለያዩ ኩነቶች ላይ ምናልባትም ደስታና ሃዘን በሚገለጽባቸው ስፍራዎች ጭምር ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ወይም ሞባይል የሚጠቀሙ ሰዎችን መመልከት የተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም የሞባይል ቴክኖሎጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ማህበረሰቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ዉስጥ እንዲያገኝ ትልቅ እድል ፈጥሮለታል፡፡ ሞባይል ከሚሰጣቸዉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች መካከል ማህበራዊ ሚዲያዎችን የመከታተልና መረጃ የማግኘት እድል መፍጠሩ ተጠቃሽ ነዉ፡፡ አሁን ላይ ተንቀሳቃሽ ስልክን በአዋቂዎች እጅ ብቻ ሳይሆን በህጻናትና በታዳጊዎች እጅ መመልከቱ እየተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ሞባይል ካልተሰጣቸዉ ምግብ የማይበሉ፤ እንቅልፍ የማይዛቸዉ፤ ሌላ ጨዋታ የማይጫወቱ ልጆችን መመልከትም እንዲሁ፡፡ ሞባይል ሳያዩ ለሰአታት ወይም ለቀናት መቆየት የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ይገመታል፡፡
ቴክኖሎጂዉ ማኅበራዊ መስተጋብርን ከማጠናከሩ እና በተለያዩ አማራጮች መረጃን በቀላሉ ለማግኘት ከማስቻሉ ባሻገር ለጥላቻ እና ለተሳሳተ መረጃ መስፋፋት እንደ በር ከፋች እየሆነ መምጣቱን ኤኤምኤን ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ወጣት ጂጄ ቀቤሳ አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቴክኖሎጂዉን በመጠቀም የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት መቀየር መቻላቸዉን ትገልጻለች፡፡
የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ፕላትፎትሞች የበርካቶችን ችግር እየቀረፈ የመጣ ዘመናዊ መገናኛ (ሚድየም) መሆኑን አጽንኦት ሰጥታለች። አቶ አለማየሁ ገዛኸኝ በበኩላቸው፣ ማህበራዊ ሚዲያ በዜጎች ላይ አዎንታዊ ጠቀሜታ እና አሉታዊ ጉዳቶችን እንደሚያስከትል ያስረዳሉ፡፡ ማኅበራዊን ሚዲያን ለበጎ አላማ የሚጠቀሙትን ግለሰቦች መደገፍ እና ለአሉታዊ አላማ የሚጠቀሙትን ደግሞ ማስተማር ጠቃሚ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ወጣት ዮናታን ጎና አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች አዎንታዊ ይዘቶችን ከመከተል ይልቅ፣ ለሚሳደቡና ሰዎችን ባልተገባ መንገድ ለሚዘልፉ ትኩረት መስጠታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ይገልጻል።
ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ አቡበከር ሙስጠፋ፣ በአሁኑ ወቅት ጥቂት የማይባሉ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ኑሮና ህይወትን ለማሻሻል የማይጠቅሙ ጉዳዮችን በመከታተል ጊዜአቸዉን በከንቱ እንደሚያሳልፉ ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በአቋራጭ ለመክበር እና ዝና ለመጎናፀፍ የሚሞክሩ ግለሰቦች ብዙ ትኩረት ማግኘታቸው ችግሩን አባብሶታል።
አንዳንድ ግለሰቦች የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት ጊዜያዊ ጥቅምን እንደሚያገኙ እና እነዚህ ይዘቶች እውነታው ሲታወቅ የሚረሱ መሆናቸውን የሚናገሩት ደግሞ አቶ መክብብ ገ/ማርያም ናቸዉ፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነውና ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ መዋቅር አስጊ የሆነው ሁኔታ ስድብና ዘለፋ የሚያበዙ ግለሰቦች የተወዳጅነትና ከፍተኛ ተከታይነት ማግኘታቸው ነው፡፡
መልካም የሚሰሩ ሰዎችን በአብዛኛው ጊዜ ተቀባይነት ሲያጡ፣ ሀገርንና ግለሰብን ማንነት ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሳደቡ፣ የሚያንቋሽሹና የሚያሳንሱ ቃላቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች ግን ብዙ ተከታይ የሚያገኙበት ሁኔታ መኖሩን ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ።

መፍትሔው የባለሙያ ጥሪና የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው ፣ዓለም በቴክኖሎጂ በተሳሰረችበት በዚህ ወቅት ቴክኖሎጂን በአግባቡ የሚጠቀም ትውልድ ያስፈልጋል የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ይህንን ለመምራት ደግሞ የአጠቃቀሙን መንገድ ማቃናት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን መምህር የሆኑት ኤልያስ ወርቁ ዶ/ር በጉዳዩ ላይ በሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በአብዛኛዉ የጋዜጠኝነትን መርህ እና ሙያን ስለማይከተል፣ ያልተጣራ መረጃ በቀላሉ እንዲሸራሸር በር ከፍቷል ይላሉ። ማኅበራዊ ሚዲያ ሁሉም ተዋናይ የሆነበት የሁሉም ተሳትፎ ያለበት መድረክ ነው።
ለጥሩ ነገር ከዋለ፣ ሀገር የመገንባት እና ማኅበራዊ ትስስርን ማላቅ ያስችላል፡፡ በተቃራኒዉ ደግሞ ለእኩይ ተግባር ከዋለ፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻን የሚዘራ ሀገር አፍራሽ ይሆናል ይላሉ፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ ያገባኛል፣ ይመለከተኛል ማለት ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው የሚሉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ በተለይ “ኢትዮጵያዊ እስከሆንኩ ድረስ ያገባኛል” የሚሉ ብዙዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሳይቃጠል በቅጠል እንደሚባለዉ አዲሱ ትዉልድ በማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተጽእኖ ስር እንዳይወቅድ፤ ባህሉን ፤ ማንነቱን፤ ሃይማኖቱንና ማህበራዊ እሴቶቹን እንዳያጣ ሁሉም ከወዲሁ ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡
በሔለን ተስፋዬ