በህፃናት ላይ የጨጓራ በሽታ እንዴት ይከሰታል? ህክምናውስ?

You are currently viewing በህፃናት ላይ የጨጓራ በሽታ እንዴት ይከሰታል? ህክምናውስ?
  • Post category:ጤና

AMN- ህዳር 24/2018 ዓ/ም

‎በልጆች ላይ የጨጓራ ህመም የሚከሰት ሲሆን፣ አንዳንዴም ከተወለዱ ጊዜ ጀምሮ በበሽታው የሚያዙበት አጋጣሚ መኖሩን ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ሀድያ ይማም ያስረዳሉ።

‎ከእናታቸው ማህፀን ገና የተወለዱ ወይም አዲስ የተወለዱ ህፃናት ላይ በተፈጥሮ የህፃናት አንጀት ጡንቻ ሲፋፋ ምግብ እንዳይተላለፍ ስለሚያደርግ በቀላል ቀዶ ጥገና ሊስተካከል እንደሚችል ዶ/ር ሀድያ ይገልፃሉ።

‎በዚህ ጊዜ በጨቅላ ህፃናት ላይ የህፃናት አንጀት ጡንቻ ሲፋፋ መከሰቱ የሚታወቀው ከተወለዱ በ21ኛ ቀናት ጀምሮ መሆኑን የሚያስረዱት ዶ/ር ሀድያ፣ በዚህ ወቅት ጨቅላ ህፃናት ላይ የሆድ መነፋት፣ የወሰዱት ወተት አለመርጋት እንዲሁም በተደጋጋሚ ማስመለስ ከታየባቸው የአንጀት ጡንቻ መከሰቱን የሚጠቁሙ ምልክቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

‎ከላይ የተዘረዘሩት ምልክቶች በጨቅላ ህፃናት ላይ ከታዩ እና ህመሙ በምርመራ ከተረጋገጠ፣ በቀላል ቀዶ ህክምና ማከም እንደሚቻልም አስረድተዋል።

‎ከዚህ በተጨማሪ እስከ አንድ ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህፃናት ላይ የሚከሰት የጨጓራ ህመም አይነት መሆሩን ገልፀው፣ የጨጓራ ህመም ወይም በተለምዶ (የአሲድ መመለስ) እንደሚባል ዶ/ር ሀድያ ያስረዳሉ። ‎ሌላው በህፃናት ላይ የሚከሰተው የጨጓራ አይነት በኢንፌክሽን ምክንያት የሚከሰት ሲሆን፣ እድሜቸው ከፍ ባሉ ህፃናት ላይ እንደሚስተዋልም ገልፀዋል ።

‎የጨጓራ ህመም በኢንፌክሽን ምክንያት የመጣ ከሆነ ማቅለሽለሽ፣ አልፎ አልፎ የሆድ ህመም እና የምግብ አለመርጋት ከሚያሳዩት ምልክቶች ውስጥ ተጠቃሾች መሆናቸውን አንስተዋል።

‎በማህበረሰቡ ዘንድ ከዚህ ቀደም ህፃናት የጨጓራ ህመም ይከሰታል ተብሎ እንደማይታሰብ የገለፁት ዶ/ር ሀድያ፣ ምልክቶቹን በማየት በምርመራ የጨጓራ ኢንፌክሽን በልጆች ላይ እየተለመደ መምጣቱን አመላክተዋል።

‎ልጆች በጨጓራ ህመም ሲያዙ በቅድሚያ የሚታየው መንስኤው መሆኑን ጠቁመው፣ ከተፈጥሮ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ከሆነ ክህምና እንደሚኖረው ይገልፃሉ። በልጆች ላይ እየተለመደ የመጣው የጨጓራ ባክቴሪያ ከሆነ ደግሞ፣ ኢራዲኬሽን ቴራፒ ሶስት አይነት መድሀኒቶችን እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል። የዚህ የቴራፒ ህክምና አይነት ረዘም ላለ ጊዜ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህ የህከምና አይነት ልጆች በአግባቡ ይታከማሉ ሲሉ ተናግረዋል።

‎ስለዚህ ወላጆች ረዘም ላለ ጊዜ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ አልፎ አልፎ የሆድ ህመም፣ ማስመለስ፣ ክብደት መቀነስ፣ በልጆቻቸው ላይ ካስተዋሉ የጨጓራ ባክቴሪያ ሊሆን ስለሚችል ወደ ህክምና ማምራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ።

‎ይሄ በሽታ ወደ ልጆች የሚተላለፈው ከአዋቂዎች መሆኑን፣ አብሮ በመብላት (በመጠጣት) እና በንፅህና ጉድለት ምክንያት እንደሚተላለፍ አስረድተዋል። ስለዚህ ንፅህናን በመጠበቅ፣ ጨጓራ የታመሙ ወላጆች አስፈላጊውን ህክምና በመውሰድ፣ በሽታው ወደ ልጆች እንዳይተላለፍ ማድረግ እንደሚቻል አስረድተዋል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review