የአፍሪካን የልማት አጀንዳ የሚመራውን የአፍሪካ ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ዋና ዳይሬክተሮች ኮሚቴ 19ኛ መደበኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ ማስጀመራቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ለአስር ዓመት የልማት ዕቅድ እና ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስኬታማነት ስታትስቲክስን በወሳኝ አቅምነት በመለየት ትኩረት ሰጥታለች ብለዋል።
የስታትስቲክስ አገልግሎት ተቋሟንም እያዘመነች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ፖለሲዎቻችን፣ የልማት ትግበራዎቻችንና ውሳኔዎቻችንን ጥራት ባላቸው መረጃዎች ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ እየሰራን እንገኛለን በማለትም አክለዋል።
የበለፀገችና ጠንካራ አፍሪካን የመፍጠር መሻታችንን በማሳካት ረገድም ስታትስቲክስ ወሳኝ ሚና አለው ነው ያሉት።
ስታቲስቲክስ የልማት ካርታችን ነው፤ የት እንዳለን ይነግረናል፣ ወዴት እንደምንሄድም ያሳየናል ሲሉም ገልጸዋል።
በመሆኑም በአፍሪካ የስታትስቲክስ ተቋማዊ ነጻነትን ማጠናከር፣ ለስታትስቲክስ ዘላቂ ፋይናንስን ማረጋገጥ እና በአህጉሪቱ ወጥነት ያለው የመረጃ ስርዓት መፍጠር ላይ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል ነው ያሉት።