ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን Cold-Formed Steel (CFS) የግንባታ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚገነቡ ቤቶች ከ60 እስከ 70 በመቶ የሲሚንቶ ፍላጎትና የአካባቢ የግንባታ ግብዓት እንደሚቀንስ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ቶማስ ደበሌ በመዲናዋ የሚከናወነውን የቤቶች ግንባታ አስመልክቶ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ አዲሱን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚገነቡ ቤቶች ከ60 እስከ 70 በመቶ የሲሚንቶ ፍላጎትና የአካባቢ የግንባታ ግብዓት እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡
በመዲናዋ የቤት ልማት ኘሮግራም ረጅም እድሜ ቢኖረውም በመፍጠርና መፍጠን ባለመመራቱ ምክንያት ከተማ አስተዳደሩ ለበርካታ ዕዳ ተዳርጎ እንደነበር አይዘነጋም ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ይህን ታሪክ ለመቀየርና አሻሽሎ ለመምራት የሥራ ባህልን ማሻሻልና ማሳደግ እንዲሁም አዳዲስ የቤት ልማት ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር በማስገባት ላይ ይገኛል፡፡
ለዚህም ከተያዘው ዓመት ጀምሮ በመዲናዋ 1ዐዐ ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ ዘርፈ ብዙ አንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በዚህ የቤት ልማት ኘሮጀክት ቀደም ሲል የቤት ባለቤት ለመሆን ገንዘብ ሲቆጥቡ የነበሩ ዜጎችን ቅድሚያ ታሳቢ ለማድረግ ታቅዷል፡፡
1ዐዐ ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ሲታሰብ 5ዐ ሺውን በመንግስትና በግለሰቦች አጋርነት እንዲሁም 5ዐ ሺውን በመንግስት አቅም ለመገንባት አስፈላጊ የሚባሉ የቴክኖሎጂ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡
የዲዛይንና የፋይናንስ ሥራዎችን በራስ አቅምና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ግንባታውን ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም መፍጠንና መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ የከተማ ልማት እንቅስቃሴን ከግብ ለማድረስ ግንባታውን በቴክኖሎጂ የማገዝ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ነው፡፡
ቴክኖሎጂው በአለም ደረጀ በርካታ ሀገሮች ሲጠቀሙበት የነበረ ቢሆንም፤ በሀገራችን ለየት የሚያደርገው ጥቅም ላይ የዋለው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ገለፀዋል፡፡
ለአገራችን የመጀመሪያ የሆነውን Cold-Formed Steel (CFS) የግንባታ ቴክኖሎጂን በመጠቀም 26 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ትላንት የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታወሳል፡፡
በበረከት ጌታቸው