ተስፋ ያጫረው የስፖርቱ ስኬትና ምስጢሩ

You are currently viewing ተስፋ ያጫረው የስፖርቱ ስኬትና ምስጢሩ

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በረጅም ርቀት ሩጫ ያስመዘገበችው ታሪክ የማይቀለበስ  ቢሆንም፣ የሀገሪቱ ስፖርት በመሰረተ ልማት እጥረት ሳቢያ ሲፈተን ቆይቷል። ነገር ግን በቅርብ ዓመታት መንግስት ለስፖርት ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ቀላል የማይባሉ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ ይህም የስፖርቱን ስኬት ወደላቀ ደረጃ ከፍ ሊያደርገው የሚችል ወሳኝ እርምጃ ነው፡፡ በዘርፉ ያሉትን ስር የሰደዱ ችግሮች ለመፍታት መሰረት የሚጥል ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት በተለያዩ ስራዎች የሚንፀባረቅ ነው። የአዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሳትን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች ዘመናዊ የስታዲየም ግንባታ ፕሮጀክቶች መጀመራቸው ወይም መጠናቀቃቸው አንደኛው ማሳያ ነው። በሌላም በኩል የወጣት ተሰጥኦዎችን ገና በለጋ ዕድሜያቸው ለይቶ በማውጣትና በማሰልጠን ላይ አድርጓል። በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ደግሞ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ አካዳሚዎችን መክፈት እና በትምህርት ቤቶች የስፖርት ክህሎትን ማጎልበት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እጥረትን ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ እያከናወነች ያለው ስራ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ ተተኪ ስፖርተኞችን በብዛት እና በጥራት ለማፍራት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም እንደዚሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ ለመፍጠር ድርሻው የጎላ ነው።

የማዕከላትና ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ አስተዳደር ልማት ዳይሬክተሩ አቶ ብርሃኑ ባዩ ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተገነቡ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እና የስፖርት ዓይነቶች ያካተቱ መሆናቸው ቀደም ሲል ከነበሩት የተለዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል። ይህም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንዲሁም ጤናው የተጠበቀ እና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የስፖርት መሰረተ ልማቱን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ወጣትና አዳጊዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ በኩል “ጉዞ 2029” የሚል ፕሮጀክት ተጀምሯል፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማ በአጭር ጊዜ ውስጥ በ2029 የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፍ ቡድን ማድረስ፣ በረጅም ጊዜ ደግሞ አዳጊዎችን አብቅቶ ጠንካራና ወጥ አቋም ያለው ብሔራዊ ቡድን መገንባት ነው፡፡

የ“ጉዞ 2029” ፕሮጀክትን ለስኬት ለማብቃት ባለሙያዎች በመላው ሀገሪቱ አዳጊዎችን ፍለጋ ተሰማርተው ከክለቦች፣ ከክልሎችና ከአካዳሚዎች ከ 1 ሺህ 200 በላይ ተጫዋቾች የምልመላው አካል እንዲሆኑ በማድረግ ነበር ወደስራ የተገባው፡፡

በሌላም በኩል ‘አንድ ኳስ ለአንድ ሰልጣኝ’ ፓይለት ፕሮጀክት በመላው ሀገሪቱ ያሉ የእግር ኳስ ችሎታ ያላቸው ከ15 እስከ 17 ዓመት ያሉ አዳጊዎች ተመልምለው የእግር ኳስ ስልጠና የሚያገኙበት ስለመሆኑም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያሳያል፡፡

ለሁለቱም ፆታዎች ተግባራዊ የተደረገው ፕሮጀክቱ ያለፉትን አራት ዓመታት በመርሃ ግብሩ የተካተቱ አዳጊዎችን ለማብቃት እየተሰራ ይገኛል። በዚህም ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰልጣኞች መካተት ሲችሉ ወደ 54 አሰልጣኞች የተሳተፉበት ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡ ሰልጣኞች የሚያስፈልጋቸው መኖሪያ፣ ምግብ እና ሌሎችም መሰረታዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶ ትኩረታቸው እግር ኳሱ ላይ ብቻ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲከናወን የቆየውና ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከ22 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን ያረጋገጠችበት ውድድር ደግሞ አዳጊዎች ላይ እየተሰራ ያለው ስራ ውጤት እያመጣ ስለመሆኑ ተስፋ ያጫረ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ኬኒያን ማሸነፏን ተከትሎ ዩጋንዳ እና ታንዛኒያን ተከትላ ሞሮኮ በምታዘጋጀው የ2026ቱ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆኗን አረጋግጣለች። የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ሲያገኝ ከ22 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ብሔራዊ ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በእግር ኳስ ስፖርት የተጀመረው ፕሮጀክት ፍሬ በማፍራት ላይ ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም ይህ ድል የእግር ኳስ ስፖርት ወዳድ ለሆነው ህዝብ የዘመናት ቁጭት በቅርቡ መልስ እንደሚያገኝ ያሳየ ነው ያሉት ከንቲባዋ “ቀይ ቀበሮዎቹ ያስመዘገቡት ውጤት ለዘርፉ የሰጠነው ትኩረት ውጤት እያፈራ መሆኑን ማሳያ ነው” ብለዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፣ ቡድኑ የመንግሥት እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ ውጤት ነው ብለው፣ መንግስት በስፖርት ዘርፍ በርካታ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን እየሰራ መሆኑን አውስተዋል፡፡ አክለውም፣ አዳጊና ህፃናትን ማዕከል ያደረገ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችም መሰራታቸውን፣ ብቁ፣ ተወዳዳሪና አሸናፊ ትውልድ ሲፈጠር የሀገር የኩራት ምንጭ መሆኑን ጠቁመው፣ ብሔራዊ ቡድኑ ያስመዘገበው ውጤት የዚሁ ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።

የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎውን ያሳካው ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ታዲያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተመረጡ 17 አዳጊዎች በኢትዮጵያ የአዳጊዎች ብሔራዊ ቡደን አባላት ውስጥ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን እንደገለፁት፣ ከተማ አስተዳደሩ እንደሀገር በቀጣይ ዓመታት በየስፖርት አይነቱ አሸናፊ ብሔራዊ ብድን ለመገንባት የተያዘውን ግብ ለማሳካታ ለአዳጊ ወጣቶች የስፖርት ስልጠና ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ነው፡፡

410 የአዳጊ ወጣቶች የስልጠና ፕሮጀክቶችን በ11ዱም ክፍለ ከተሞች በማቋቋም በ21 የስፖርት አይነቶች ከ22 ሺህ በላይ አዳጊዎች መደበኛ የስፖርት ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ አቶ በላይ አሳውቀዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ብቻ በመዲናዋ 1 ሺህ 530 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በመገንባት ተተኪ ስፖርተኞችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት ምቹ መደላድል መፈጠሩን የቢሮ ኃላፊው ያስረዳሉ።

የ‘አዲስ ተስፋችን እግር ኳስ ፕሮጀክት’ አሰልጣኝ መሐመድ ናስር እንዳስረዱት የመዲናዋ ወጣቶች ደረጃቸውን በጠበቁ መጫወቻ ሜዳዎች በሚኖሩበት፣ በሚማሩበትና በሚሰሩበት አካባቢ በስፖርት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በየአካባቢው በብዛትና በጥራት መኖር ለአዳጊ ፕሮጀክቶች የወጣቱን ጤንነት በመጠበቀ፣ አካል ለመገንባት፣ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለስፖርት ዘርፍ የሰጠው ትኩረት በሀገሪቱ ስፖርት ታሪክ ወሳኝ ምዕራፍ ሊሆን የሚችል ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው። አሰልጣኙ እንደሚገልፁት የመንግስትን ጥረት ዘላቂና የበለጠ ፍሬያማ ለማድረግ ሊሰሩ ይገባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች ያብራራሉ፡፡ የግል ባለሀብቶች ወደ ስፖርት ኢንቨስትመንት እንዲገቡ ማበረታታት እና ግልጽ የሆኑ የአጋርነት ስርዓቶችን መዘርጋት። እንደዚሁም የስፖርት ተቋማትን አመራር በስፖርት ዕውቀት እና በሙያዊ ብቃት ለተመረጡ ሰዎች ብቻ መተው ይገባል ይላሉ።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review