በአምባሳደር ጄነራል ባጫ ደበሌ የተፃፈው ”የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ” መፅሐፍ ተመረቀ

You are currently viewing በአምባሳደር ጄነራል ባጫ ደበሌ የተፃፈው ”የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ” መፅሐፍ ተመረቀ

AMN ኀዳር 27/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የጦር መኮንኖች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስምና ልምድ ያካበቱት አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ በወታደራዊ ልምዳቸውና ጥልቅ ጥናት ላይ የተመሰረተውን ”የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ” መፅሐፋቸውን አስመርቀዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የፌዴራልና የክልል የፀጥታ አመራሮች ጄነራል መኮንኖች የመከላከያ የክብር አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነው በመከላከያ መኮንኖች ክበብ በደማቅ ስነ-ስርዓት መፅሃፉ የተመረቀው።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ የተሰነደ የፀረ ሽምቅ ውጊያ ማኑዋል የነበራት ቢሆንም የተሻሻለ እንዳልነበረ አውስተው ”የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ” መፅሐፍ ግን ዘመኑን የሚመጥንና ለጦር መሪዎች ማስተማሪያነት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

ጄኔራል ባጫ ደበሌ ይህንን ጠቃሚ መፅሐፍ በማበርከታቸውም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ምስጋና አቅርበዋል።

ብዙ የኛ ሀገር ጦር መሪዎች የሚፅፉት መፅሐፍ ታሪክ ላይ ያተኩራል። ”የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ” መፅሐፍ ግን ሳይንሳዊ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ይህንን በተግባር ያረጋገጡት ደግሞ ጄነራል ባጫ ናቸው ብለዋል።

በ187 ገፆች የተቀነበበውና በአምስት ምዕራፎች የተከፋፈለው ”የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ” መፅሐፍ ስለሽምቅ ውጊያ ዳራና ልምድ የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ዓለምአቀፍ ተሞክሮዎች የሸማቂና የአሸባሪ ቡድኖች ባህሪ የፀረ-ሽምቅ ውጊያና የፀረ-ሽምቅ ግብረ-ኃይል ዝግጅትን ምንነት የሚገልፅ መሆኑን ከሃገር መከላከያ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review