ሁሉንም የአሠራር ሒደቶች በአንድ ስርዓት ያቀፈ አዲስ ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ እንደተናገሩት፣ ከተማ አስተዳደሩ ፍትሐዊ አገልግሎት ለመስጠት ዲጂታል ስርዓቶችን በመዘርጋት ላይ ይገኛል። አዲሱ ቴክኖሎጂ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከዚህ በፊት የነበሩ ማነቆዎችን የሚፈታ እና ዘርፉን የሚያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተቀናጀ አገልግሎት ለማሳለጥ የሚያስችለውን አዲሱን ቴክኖሎጂ ለቢሮው ያበለጸገው የአዲስ አበባ ከተማ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ መሆኑም ተገልጿል።

ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ በመዲናዋ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ብዛት፣ የሚያመርቷቸውን ምርቶች፣ የሚፈልጉትን ግብዓት እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በመለየት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መነቃቃትን ይፈጥራል ተብሏል።

ምክትል ከንቲባው አክለውም፣ ቴክኖሎጂው ጊዜና ጉልበትን በመቆጠብ የምዝገባ አገልግሎቶችን ኦንላይን የሚሰጥ፣ የአገልግሎት ጥያቄን በቀጥታ መከታተል የሚያስችል እንዲሁም ለመረጃ ተደራሽነት፣ ግልጽነት እና ትክክለኛነት አጋዥ መሆኑን አስረድተዋል።
ቴክኖሎጂው 12 ሞጁሎችን፣ 18 ዋና አገልግሎቶችን እና 40 ንዑስ አገልግሎቶችን የያዘ ሲሆን፣ ይህም የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ነው።
በራሔል አበበ