የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2027 የሚካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ የCOP32 ጉባኤንና 27ኛውን የኢንተርፖል የአፍሪካ ቀጠና ኮንፈረንስ፣ እ.ኤ.አ በ2028 የሚካሄደውን 96ኛውን የኢንተርፖል ጠቅላላ ጉባኤ እና ሌሎች አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች በስኬት እንዲከናወኑ ሥራውን መምራት የሚያስችል ዝግጅት በዋናው መሥሪያ ቤት ስትራቴጂክና ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች በተገኙበት ይፋ አድርገዋል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ ዝግጅቱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ጉባኤዎቹ የሀገሪቱን መልካም ገጽታ አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ እንዲካሄዱ ለማስቻል ሁለንተናዊ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ በስፋትና በጥራት የማዘጋጀት፣ ተጨማሪ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችና ትጥቆችን በስፋትና በጥራት በማደራጀት ሰፊ የሎጂስቲክስ እና የቴክኖሎጂ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ የመገንባት፣ የፖሊስ ታሪካዊ ዳራን የሚያሳይ አውደ ርዕይ በዓይነትና በዲጅታል የማዘጋጀት፣ ፖሊስ ለፖሊስ የውጭ ግንኙነትና የትብብር ሥራዎችን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች እንዲከናወኑ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል አያይዘውም ሥራዎቹ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አንስተው ዝግጅቱን የሚመራ የፖሊስ ኃይል የተደራጀ መሆኑን መግለጻቸዉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡