በተጨዋችነት ዘመኑ ከሊቨርፑል፣ ሪያል ማድሪድና ባየርን ሙኒክ ጋር የተሳካ ጊዜን አሳልፏል፡፡
ከሀገሩ ስፔን ጋርም ቢሆን አንድ የዓለም ዋንጫና ሁለት የአውሮፓ ዋንጫዎችን አንስቷል ዣቪ አሎንሶ፡፡
ጫማ ሰቅሎ አሰልጣኝነትን ለጀመረበት ባየር ሊቨርኩሰን ውለታ ሰርቷል፡፡ ክለቡን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቡንድስሊጋ ዋንጫ አሸናፊ ያደረገው የ44 ዓመቱ ዣቪ አሎንሶ ነው፡፡
በጀርመን ያስመዘገበው ስኬት የሊቨርፑልን ቀልብ ስቦ የየርገን ክሎፕ ምትክ እንዲሆን ቢታሰብም ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቀሩ፡፡
ባለፈው ዓመት መባቻ ካርሎ አንቼሎቲን ተክቶ ማድሪድን የተረከበው ዣቪ አሎንሶ ከስድስት ወራት በኋላ ወንበሩ ተነቃንቋል፡፡ ሎስ ብላንኮዎቹ ካለፉት አምስት የላሊጋ ጨዋታቸው ያሸነፉት አንድ ብቻ ነው፡፡
ከትናንት በስቲያ በላሊጋው በሴልታቪጎ 2ለ0 መሸነፋቸው የማድሪድ ቦርድ አባላትን አስቆጥቷል፡፡
ከመሪው ባርሴሎና በአራት ነጥብ አንሶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ክለቡ ትናንት አመሻሽ በጠራው ድንገተኛ ስብሰባ ውጤቱን እንዲያሻሽል ለአሰልጣኙ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡
ማድሪድ ነገ ምሽት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከማንችስተር ሲቲ ጋር በሳንቲያጎ በርናቢዩ ይጫወታል፡፡
የ15 ጊዜ የባለ ትልቁ ጆሮ ዋንጫ አሸናፊ ማድሪድ አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ‹‹ሁላችንም በተመሳሳይ ጀልባ ላይ ነን ፣ በመጥፎም በጥሩም ስሜት ውስጥ እያለፍን ነው፣ የነገው ጨዋታ እጅግ በጉጉት የምንጠብቀው ነው›› ብሏል ለቢቢሲ ስፖርት፡፡
ነገ ማድሪድ በሜዳው ከተሸነፈ ዣቪ አሎንሶ ሻንጣውን ሸክፎ እንደሚወጣ የስፔናዊ እውቅ ጋዜጠኛ ጉሌም ባላጉ ሪፖርት ጠቁሟል፡፡
የማድሪድ ፕሬዚደንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ባለፈው ሳምንት ለብቻቸው ጠርተው እንዳናገሩት፤ በተለይ ከተጨዋቾች ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት እንዲያስብበት ማስጠንቀቃቸውን ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል፡፡
አሎንሶ ግን ‹‹ ንግግራችን እንደቀጠለ ነው፣ ከተጨዋቾቼ ጋር መልካም ግንኙነት አለኝ›› ነው ያለው፡፡
የአሎንሶ ፈላጊ ሊቨርፑልም ከወቅቱ አሰልጣኙ አርን ስሎት ጋር ረጅም ጉዞ የሚጓዝ አይመስልም፡፡
ኔዘርላንድሳዊ አሰልጣኝ ከክለቡ አርማ ሞሀመድ ሳላህ ጋር የገቡት እሰጥ ገባ ሌላኛው ሰሞነኛ አጀንዳ ሆኗል፡፡
ወደ ሊቨርፑል ልትመለስ ትችላለህ? ተብሎ ከቢቢሲ ስፖርት ጥያቄ የቀረበለት አሎንሶ ‹‹እውነት ለመናገር ከቀድሞ ክለቤ ጋር እገናኛለሁ፣ አሁን ግን ቦታዬ ማድሪድ ነው፣ ለወደፊት ምን እንደሚሆን ዛሬ ላይ ሆኖ መገመት አዳጋች ነው›› ብሏል ጫና ውስጥ የሚገኘው ዣቪ አሎንሶ፡፡
በውድድር ዓመቱ 26 ግቦችን ያስቆጠረው ክሊያን ምባፔ በነገው ጨዋታ የመግባት እድሉ ጠባብ ነው ተብሏል፡፡
ዛሬ ከቡድኑ ጋር ልምምድ ያልሰራው ፈረንሳዊ አጥቂ ከነገው ጨዋታ ውጭ የመሆን እድል አለው፡፡
ከምባፔ በተጨማሪ ኤደር ሚሊታኦ፣ ትሬንት አሌክዛንደር አርኖልድ፣ ዳኒ ካርቫል፣ ዲን ሃውሰንን እና ዴቪድ አላባ በህክምና እርዳታ ላይ ስለሚገኙ የኢትሃዱን ክለብ ጫና መቋቋም ሊያዳግተው እንደሚችል ዘገባው አክሏል፡፡
ዣቪ አሎንሶ ጠንካራውን ማንችስተር ሲቲን አሸንፎ የተነቃነቀውን ወንበር ያረጋጋ ይሆን? ወይስ ተሸንፎ ጉሌም ባላጉ እንዳለው ከበርናቢዩ ይሰናበት ይሆን? ነገ ምሽት የሚደረገው ጨዋታ ሲጠናቀቅ መልስ ያገኛል፡፡
በታምራት አበራ