የኢትዮጵያ የኃይል ምርት እና አጠቃቀም ስርዓት ለቀጣናው እና ለአፍሪካ መትረፍን አላማ ያደረገ ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ የኃይል ምርት እና አጠቃቀም ስርዓት ለቀጣናው እና ለአፍሪካ መትረፍን አላማ ያደረገ ነው

AMN ታህሳስ 1/2018

ኢትዮጵያ የኃይል አመራረት፣ ስርጭት እና አጠቃቀም ስርዓቷን ከሀገር አልፎ ለቀጣናው እና ለአፍሪካ መትረፍን አላማ ለማድረግ እየሰራች እንደምትገኝ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

የአፍሪካ ሕብረት ያዘጋጀው የአፍሪካ የኃይል አጠቃቀም ውጤታማነት ኮንፈረንስ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ኮንፍረንሱን በጋራ ከፍተዋል።

የአፍሪካ ህብረት ያዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የኃይል አጠቃቀም ውጤታማነት ኮንፍረንስ (Energy Efficiency Conference) በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ዛሬ ተጀምሯል።

ኮንፍረንሱ እ.አ.አ በ2024 በአዘርባጃን ባኩ በተካሄደው 29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 29) ይፋ የተደረገው የአፍሪካ ኢነርጂ ውጤታማነት ጥምረት ማዕቀፍ ስር የሚካሄድ ነው።

“የአፍሪካ የኢነርጂ ውጤታማነት አጀንዳን በስትራቴጂካዊ አጋርነት ውጤታማ ማድረግ” የኮንፍረንሱ መሪ ሀሳብ ነው።

አህጉራዊው ሁነት የተዘጋጀው የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተቋም በሆነው የአፍሪካ ኢነርጂ ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር ነው።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በመድረኩም ላይ ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ የኃይል አመራረትና አጠቃቀም ስኬታማነት እያደረገችው ስለምትገኘው ጥረት ተሞክሮ ማካፈሏን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የኃይል አመራረት፣ ስርጭት እና አጠቃቀም ስርዓት ለታዳሽ የኃይል አማራጮች ቅድሚያን የሚሰጥ፣ ኢነርጂን በማምረት ሂደት ሊፈጠር የሚችል የአየር ንብረት ተፅእኖን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆኑን አመልክተዋል።

እንዲሁም መሰረቱን በጋራ ተጠቃሚነት ላይ አድርጎ ለአህጉራዊ ትስስር እና ዘላቂ ልማት ከፍተኛ አስተዋዕፆ ማበርከትና ለጎረቤት ሀገራት ጭምር መትረፍን ግቡ አድርጎ ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆነም ተናግረዋል።

በበርካታ የኃይል አማራጮች የተሞላችው አፍሪካም የኃይል ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በተሰናሰለ ሁኔታ አካባቢያዊ ስነምህዳርን ከግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ ኃይልን ማመንጨት ይገባል ነው ያሉት።

የተመረተውን ኃይል በውጤታማነት ማሰራጨትና መጠቀም እኛ አፍሪካዊያን በቀጣይ ትኩረት ሰጥተን በትብብር ልንሰራውና ልምድ ልንለዋወጥበት የሚገባ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል አቶ አደም።

ኮንፍረንሱ የኢነርጂ ውጤማነትን በማረጋገጥ የአፍሪካ ኢኮኖሚ እድገት፣ ዘላቂ ልማት እና ለአየር ንብረት ለውጥ የተግባር ምላሽ አቀጣጣይ ሞተር የማድረግ አላማ ያለው መሆኑ መገለጹን ተዘግቧል፡፡

የመጀመሪያው የአፍሪካ ኃይል አጠቃቀም ውጤታማነት ኮንፍረንስ እስከ ነገ ይቆያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review