ኢትዮጵያና ዛምቢያ በወታደራዊ መስክ በትብብር ለመሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ተፈራረሙ።
ስምምነቱ ለረጅም ዓመታት የቆየውን የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከርና በልዩ ልዩ ወታደራዊ መስኮች ለጋራ ተጠቃሚነት መሥራትን ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም መሠረት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከዛምቢያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄፍሪ ዚኤሌ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ፤ በየተዋረድ ያሉ የየሀገራቱ የመከላከያ አመራሮች የስምምነት ፊርማ ማከናወናቸው ተጠቁሟል።
በዚሁ ወቅትም ለቀጣናው ደኅንነት እንዲሁም ለሀገራት ሠላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አስገንዝበዋል።
ከዛምቢያ ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ እንሠራለን ማለታቸውንም የመከላከያ ኦንላን ሚዲ ለኢዜአ የላከው መረጃ አመላክቷል።
የዛምቢያው ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናል ጄነራል ጄፍሪ ዚኤሌ በበኩላቸው፤ ትብብራችን የተሻለ ዐቅም ለመፍጠርና የጋራ ጥቅማችንን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።
ከዓድዋ ጦርነት ጀምሮ ያለውን የኢትዮጵያን ሠራዊት ልምድና ተሞክሮ እንዲሁም የኢትዮጵያውያንን የጀግንነት ሥነ-ልቦና አድንቀው፤ ይህም በትብብር እንድንሠራ ያነሳሳን ነው ብለዋል።
በልዩ ልዩ ወታደራዊ መስኮች በጋራ ለመሥራት ዛምቢያ ያቀረበችውን ጥያቄ ኢትዮጵያ በመቀበሏ መደሰታቸውንም ጠቁመዋል።
የሁለቱን ሀገራት ኤታማዦር ሹሞች ውይይት ተከትሎ የመከላከያ ሚኒስትር ዴዔታ ማርታ ሉዊጂ ከዛምቢያ አቻቸው ማምቦ ሃማውንዱ ጋር በዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ፣ በደኅንነት፣ በወታደራዊ ትምህርትና ሥልጠና፣ በወታደራዊ ኢንዱስትሪና በሌሎችም ዘርፎች በጋራ መሥራት የሚያስችል የስምምነት ፊርማ አድርገዋል።
ወይዘሮ ማርታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የስምምነቱ ዋነኛ ዓላማ የሁለቱን እህትማማች ሀገራት ብሔራዊ ፍላጎት ለማስጠበቅና የጋራ ተጠቃሚነትን የበለጠ ለማሳደግ ነው።
የዛምቢያ መከላከያ ሚኒስትር ዴዔታ ማምቦ ሃማውንዱ በበኩላቸው፤ ለመከላከያ ዘርፋችን ስኬት በሁሉም የትኩረት ዘርፎቻችን ያለንን ግንኙነት አጠናክረን እናስቀጥላለን ብለዋል።