አዲስ አበባ ከተማን ለማስዋብና ገጽታዋን ለመቀየር 24/7 በተሰራው ሥራ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ እና ትብብር የታየበት በዚህም ከፍተኛ ለዉጥ መታየቱን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ አዲስ አበባ ከተማን ለማስዋብ እና ገጽታዋንም ለመቀየር የተተገበረውን የልማት ሥራ አስመልክቶ “ከብሪክስ አፍሪካ ቻናል” ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም፣ አጠቃላይ የከተማዋን ገፅታ በመሠረታዊነት ስለቀየረው አካታች የልማት ሥራ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በማብራሪያቸው፣ መንግስት ከመነሻው አዲስ አበባ ከተማን መልሶ የማልማት፣ የማስዋብ፣ የማጽዳት እና ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረግ ትልቅ ፍላጎት እንደነበረው ገልጸዋል፡፡
ለዚህም “ገና ወደ ምርጫ ሳንገባ አዲስ አበባ ከተማን እንደ ስሟ ውብ አበባ እናደርጋታለን ብለን ለህዝቡ ቃል ገብተን ነበር” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ ውብ አበባ እንድትመስል የዛሬ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ከጥንትም ስሟ ሲሰየም ምኞት እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ፣ ነገር ግን ከተማዋ እንደስሟ ሳትሆን መቆየቷን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም መንግስት እሰራለሁ ብሎ ቃል በገባው መሠረት አስፈላጊ ጥናቶችን አካሂዶና እና ሕዝብንም አውያይቶ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን ለማከናወን ውሳኔ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡
ጥናቱን መሠረት በማድረግም እርጅና የተጫናቸውን ድሮ የተሰሩ ቤቶችን መልሶ ለማልማት፣ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማቶችን ማከናወን መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የማይቻል የሚመስለውን ከባድ ሥራ በከተማዋ በጀት እና በበርካታ በጎ ፈቃደኛ ዜጎች እንዲሁም በአጠቃላይ በሕዝቡ ትብብር እውን ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በተለይም ከተማዋን የማስዋብና ገጽታዋን የመቀየር ሥራ 24/7 የሚሰራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሌሊት ሥራ በሚሰራበት ወቅት ህዝቡ በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡
ከአሁን ቀደም በወንዞች ዳርቻ አካባቢ ይኖሩ የነበሩና ወደ ሌላ ቦታ የተዛወሩ አንዳንድ የመዲናዋ ነዋሪዎችም፣ ከስፍራው ከመነሳታቸው በፊት አካባቢው ቆሻሻ የሚበዛበት፣ የጎርፍ እና የናዳ ስጋት የበዛበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
እንዲሁም በቂ መጸዳጃ እና በቂ የቆሻሻ ማስወገጃ የሌለበት በጣም አስቸጋሪ የሆነ ቦታ እንደነበር ያነሱት ነዋሪዎቹ፣ አሁን የተሰጣቸው ቦታ በጣም የተሸለ በመሆኑ ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በታምራት ቢሻው