የባለቅኔው የምጥቀት አክናፍ

You are currently viewing የባለቅኔው የምጥቀት አክናፍ

በባለቅኔ ጸጋዬ ገብረ መድህን ህይወትና ሥራዎች ዙርያ ከተጻፉ መጽሐፍት መካከል ‘ምጥቀት በቅኔ አክናፍ’ የተሰኘው መጽሐፍ በእጅጉ ይለያል። የመጽሐፉ ደራሲ ፋሲል ይትባረክ ውብ በሆነ አተራረክና የቋንቋ አጠቃቀም ከሽኖ ያቀረበው መጽሐፍ መሆኑ፤ የሎሬቱ የፈጠራ ሥራዎች ከህይወቱና ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር እያናበበ መተርጎሙ ብቻ አይደለም ለየት የሚያደርገው፡፡ በዋናነት የህይወት ታሪክ መጽሐፉ እንዲጻፍ የደራሲ ፋሲል መሻት ብቻም ሳይሆን የሎሬቱም መሻት ያለበት መሆኑ፣ ጸጋዬም ሳይሰስት ስለ አስተዳደጉና ህይወቱ የተረከበት መሆኑ መጽሐፉን ለየት ያደርገዋል፡፡

‘ምጥቀት በቅኔ አክናፍ’ የህይወት ታሪክ መጽሐፉ በራሱ በጸጋዬ ጠያቂነትና ፍላጎት የተጀመረ ነው፡፡ ጸጋዬ ከልጅነቱ አንስቶ እስከ 1966ቱ አብዮት ድረስ ስለነበረው ልጅነቱ፣ ስለአስተዳደጉ፣ ስለትውልድ ስፍራው፣ ስለቤተሰቦቹ፣ ስለ ትምህርት ቤት ህይወቱ፣ ስለ ከያኒነቱ፣ ስለ ትዳር ህይወቱ… በራሱ አንደበት፣ ራሱ ባለበት ሪከርድ ተደርጎ በኋላም በመጽሐፍ መልክ የተሰናዳ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡

እዚህ’ጋ ግን መጽሐፉን አንብበን ስንጨርስ በአንድ ነገር ማዘናችን አይቀርም፤ ጸጋዬ በወርሃ የካቲት 1998 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ በተለይ በአብዮቱ ሰሞን፣ ከአብዮቱ በኋላ ያሉ የህይወትና የጥበብ ስራዎቹ ሁናቴ በራሱ አንደበት ተተርኮ ለማንበብ አልታደልንም፡፡ ደራሲው ፋሲል በየሳምንቱ ኒውዮርክ በሚገኘው የጸጋዬ ቤት ሪከርደሩን ይዞ እየጠየቀ በነበረበት ሂደት ነው ሥራው ሳይቋጭ ጸጋዬ ህይወቱ ያለፈው፡፡ በዚህ ምክንያት ጸጋዬ ከአብዮቱ በኋላ ስለነበረው ሁናቴ ከአንደበቱ ለመስማት አለመታደላችን ትንሽ ቁጭት ነገር ይፈጥራል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ደራሲው ይህን ክፍተት ለመሙላት ያደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡

ገና በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ፀጋዬ ለልጆቹ ምን አይነት አባት እንደነበር በልጆቹ አንደበት ይነገረናል፡፡ በጣም ደስ በሚያሰኝ ሁናቴ ጸጋዬ በልጆቹ አንደበት ስለ አባትነቱ፣ እነዚያን አስደናቂ ቅኔዎች በምን አይነት ሁኔታ ላይ ሆኖ ይጽፍ እንደነበር፣ በአደባባይ የሚታወቀው ጸጋዬ ቤት ውስጥ ምን አይነት አባት እንደሆነ ከልጆቹ አንደበት እናነባለን፡፡

እዚህ’ጋ ማስታወስ የሚያስፈልገው አንድ ጉዳይ ‘ምጥቀት በቅኔ አክናፍ’ ትርጉም ስራ መሆኑ ነው፡፡ ደራሲ ፋሲል ይትባረክ ጸጋዬ ባረፈ ማግስት ‘Soaring on Winged Verse’ በሚል ርዕስ የጸጋዬን የህይወት ታሪክ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፎ እዚያው አሜሪካ ሀገር አሳትሞ ለንባብ እንዲበቃ አድርጓል፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈልጎ የሚገኝ መጽሐፍ አልነበረም፡፡ ታዲያ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በራሱ በደራሲው ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ለንባብ መብቃቱ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ትልቅ አበርክቶ ነው፡፡

ታምረኛዋ ጎሮምቲ

ከአምቦ በስተምዕራብ ሃያ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቦዳ በምትባለው መንደር ውስጥ ነው ጸጋዬ የተወለደው። የተወለደበት ሰሞን (የካቲት 11 ቀን 1928 ዓ.ም) ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ከባድ ጦርነት የሚካሄድበት ወቅት ነበር፡፡ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርሮ ኢትዮጵያውያንን በግፍ እያሳደደ የሚገድልበት አስጨናቂ ጊዜ ነበር፡፡ የእነጸጋዬ መንደር ቦዳ በተለይ በባንዳዎች ዝርፊያና ጥፋት በከፍተኛ ደረጃ ተጠቂ ሆነች፡፡ ጥቃቱ ወደ ጨቅላው ጸጋዬ ቤትም ደረሰ፡፡ ባንዳዎች የእነ ጸጋዬን ቤት ከመዝረፍ የተሻገረ ጥቃት ፈጸሙ። የእነ ጸጋዬን ቤት ከዘረፉ በኋላ እሳት ለቀቁበት፡፡ ወይዘሮ ፈለቀችም የጨቅላው ልጃቸውን ህይወት ለማትረፍ እየተጣደፉ ቤታቸው ዶግ አመድ ሲሆን በቁጭት ተመለከቱ፡፡

 የቤቱ አባወራ አቶ ገብረ መድህን ደግሞ በዚህ ጊዜ ከከሃዲ ባንዳዎች መሳሪያ በመግዛት በድብቅ ለአርበኞች የማስተላለፍ ሥራ ይሰሩ ነበር። ከቤታቸው ርቀው በመሄድ ነበር ይሄን ተግባር የሚከውኑት፡፡ ጨቅላው ልጃቸውና ሚስታቸውን ትተው የሄዱት አቶ ገብረ መድህን ቦዳ ውስጥ ምን እየተከሰተ እንዳለ አያውቁም። ነገር ግን ርቀው ከመሄዳቸው በፊት ለሚስታቸው ለወይዘሮ ፈለቀች የፋሺስት ወታደሮችና ባንዳዎች ቦዳ ድረስ ከዘለቁ፣ ጠላት ለመግባት ወደ ማይደፍራት ወደ ገጠራማዋ ጎሮምቲ እንድያመሩ አስቀድመው አስጠንቅቀዋቸዋል፡፡ ጎሮምቲ የአቶ ገብረ መድህን ወንድሞች የሚኖሩባት የገጠር መንደር ነች፡፡ ወይዘሮ ፈለቀችም ጨቅላው ልጃቸውን አዝለው ወደ ገጠራማዋ ጎሮምቲ ተሰደዱ፡፡

ጸጋዬ ቦዳ ቢወለድም ልጅነቱና የልጅነት ትውስታው ሁሉ ከጎሮምቲ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ጎሮምቲን እንደ “የምድር ገነት” አድርጎ ይመለከታታል፡፡ አስደናቂ መልክዓ ምድርና ተፈጥሮ የታደለች ሥፍራ ነች፡፡ ጸጋዬም የጎሮምቲን አፈር ፈጭቶ፣ ጭካ አቡክቶ አድጓል፡፡ የጎሮምቲ እረኞችን እየተከተለ ተጫውቷል፡፡ ከሾላ ዛፍ ላይ እየተንጠለጠለ በጣፋጩ የሾላ ፍሬ ሆዱን ሞልቷል፡፡ ሕጻኑ ፀጋዬ “የምድር ገነት” ብሎ በሚጠራት ጎሮምቲ ውስጥ ልጅነቱን አሳልፏል፡፡

በዚህ መሃል ግን አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ፡፡ ክስተቱ ህጻኑ ጸጋዬ ብዙም አልወደደውም፡፡ የምድር ገነት ከምትባለው ጎሮምቲ ህይወቱን የምትነጥለው መስሎ ስለተሰማው አጋጣሚው አልተመቸውም፡፡ ከወደ መንዝ የመጡ ሦስት ሰዎች በድንገት የጎሮምቲን ህይወቱን እንደነጠቁት ተሰምቶታል፡፡ እነዚህ ከመንዝ የመጡት ሶስቱ ሰዎች ከፋሽስት ጣሊያን ወታደሮች ግድያ አምልጠው ከመንዝ ወደ ጎሮምቲ የመጡ ናቸው፡፡ ሶስቱ ሰዎች የሚያገለግሉባት የነበረችው አንኮበር ከተማም በጣሊያን ወታደሮች መቃጠሉን ተከትሎ ነው የጸጋዬ የትውልድ መንደር የዘለቁት፡፡

እነ ጸጋዬ ቤት የመጡት ሶስቱ እንግዳ ሰዎች የእናቱ የወይዘሮ ፈለቀች ዘመዶች ናቸው፡፡ አንኮበር ላይ የታወቁ ካህናትና ሊቅ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ፈለቀችም ዘመዶቻቸውን በቻሉት ሁሉ ተንከባክበው ያዙዋቸው፡፡ እንግዶቹም ፈለቀችን ለማስደሰት አንድ ውለታ ለመዋል አሰቡ፡፡ በአስጨናቂ ጊዜ የወለዱት ተወዳጁ ልጃቸው ጸጋዬን የግዕዝ ቋንቋና ቅኔን ለማስተማር ወሰኑ። ሕጻኑ ጸጋዬም በታምረኛዋ ጎሮምቲ መንደር ውስጥ በአባቱ ዘመዶች በኩል የኦሮሞን ባህልና እሴቶች በእናቱ ዘመዶች በኩል ደግሞ የግዕዝ ቋንቋና ቅኔን መማሩን ቀጠለ፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ህጻኑ ጸጋዬ ከሚወደው ጨዋታ መነጠሉ በጣም አናድዶታል፡፡ ትንሹ ጸጋዬም ገና ትምህርት ቤት ደጃፍ ሳይረግጥ በጎሮምቲ ቤቱ ውስጥ በግዕዝ ቋንቋ መንፈሳዊ ምንባቦችን በቃሉ ከማነብነብ የተሻገረ ዕውቀት ገበየ፡፡ ከኦሮምኛ ቋንቋ ውጭ በማይነገርባት ጎሮምቲ ውስጥ አማርኛና ግዕዝ ገና ትምህርት ቤት ደጃፍ ሳይረግጥ በህጻን ዕድሜው ለማወቅ ቻለ፡፡

የጎሮምቲው ትንሹ ልጅና ጃንሆይ የተገናኙ ዕለት

ጸጋዬ ኋላ ላይ ከትውልድ መንደሩ ርቆ አምቦ አስኳላ ትምህርት ቤት ሲገባም በልጅነቱ የተማረው የግዕዝ ቋንቋና ቅኔ በድርሰት የትምህርት ክፍለ ጊዜ ውስጥ ጎልቶ መታየት ጀመረ፡፡ በተለይ የሚጽፋቸው ግጥሞች ከእድሜው እጅግ የተሻገሩ በመሆናቸው በመምህራኑ ሳይቀር የሚደነቅ ልጅ ሆነ፡፡ ከሥነ ጽሑፍ ባሻገር በተውኔት አዘጋጅነትና ተዋናይነት ጭምር ትንሹ ጸጋዬን የሚተካከል ሌላ ተማሪ አልነበረም፡፡

ይሄ የተዋናይነትና አዘጋጅነት ጥልቅ መሻቱ ግን አንድ አስገራሚ ክስተት ይዞ መጣ፡፡ አምቦን አዘውትረው የሚጎበኙት ንጉሰ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ ከተማዋ የመጡበት ሰሞን ነው ክስተቱ የተፈጠረው፡፡ ንጉሱ ጸጋዬ የሚማርበት የአምቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሊጎበኙ እንደሆነ አስቀድሞ ተሰማ። የ13 ዓመቱ ጸጋዬም አንድ ነገር አሰበ። “ሪደር ሲክስ” የተባለው የእንግሊዘኛ መማሪያ መጽሐፍ ውስጥ የሚያውቀው “ኪንግ ዲዮኖስየስ ኤንድ ሂዝ ቱ ብራዘር” የተሰኘ ቴአትር ለዚያን ሰዓት በሚያመች መንገድ አድርጎ ለማቅረብ አሰበ፡፡ ከዚያ በፊት ተውኔት ጽፎም ሆነ መድረክ ላይ ተውኖ የማያውቀው ጸጋዬ በተውኔቱ ላይ የሚተውኑ ጓደኞቹን መረጠ። አንዱ የክፍል ጓደኛው ደሬሳ ነበር። ነገር ግን ጓደኞቹ የጸጋዬን ሃሳብ እንደ እብደት ቆጠሩት፡፡ ጸጋዬ ግን ተከራክሮ አሳመናቸውና አዳራቸውን ሲለማመዱ አድረው በማግስቱ በጃንሆይ ፊት ለማቅረብ ወሰኑ፡፡ ይሄ ሁሉ ዝግጅት ሲያደርጉ ግን ተውኔቱ መድረክ ላይ መቅረብ አለመቅረቡን የሚወስኑት የትምህርት ቤቱ መምህራንና ኃላፊዎች ስለ ተውኔቱ አንዳችም ነገር አያውቁም፡፡ ጸጋዬ ግን “እሱን እኔ አሳምናለሁ” በማለት ቁርጠኛ አቋም ያዘ፡፡

በማግስቱ ጠዋት፤ የእንግሊዝኛ ትምህርት እንደተጀመረ “እኔና ጓደኞቼ ለጃንሆይ የሚቀርብ ቴአትር አዘጋጅተናል” ሲል ጸጋዬ ለመምህሩ ለሚስስ ኸቺንግስ አስታወቀ፡፡

“የምን ቴአትር ነው ጸጋዬ?” ስትል ጠየቀችው፡፡

“ንጉስ ዲያኖስየስና ሁለቱ ወንድማማቾች”

ሚስስ ኸቺንግስ ጉዳዩ ብዙም አላጓጓትም፡፡ እምቢ ያለች ባትመስልም በዘዴ ጥያቄያቸው ችላ ለማለት ወስናለች። ጸጋዬ እሷን ለማሳመን ከቴአትሩ ለቅምሻ የሚሆን ነገር ለማሰማት እንደሚችሉ ነገራት፡፡ አስተማሪዋ በመፍቀድ ባለመፍቀድ መሃል እየዋለለች፣ ጸጋዬ ጓደኞቹን በጥቅሻ እንዲነሱ አዘዛቸው። ሶስቱም ተነስተው አዳር ካጠኑት ተውኔት ውስጥ ቀንጭበው ክፍል ውስጥ በመነባንብ መልክ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ የክፍል ተማሪዎች በጓደኞቻቸው ችሎታ ተደምመው በተመስጦ ይመለከታሉ፡፡ ሚስስ ኸቺንግስም እያየችው ባለው ነገር እጅግ ተገረመች፡፡

በልቧ ‘ይሄ ቴአትርማ መቅረብ አለበት’ ብላ ወሰነች፡፡ እነ ጸጋዬ ቴአትሩን እያቀረቡ ከፊት የተቀመጠውን ተማሪ በጆሮው የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የሆነው ባሏን “በፍጥነት ና በለው” አለችው፡፡ ዳይሬክተሩ ሳይቆይ መጣና በሥጋት “ምን ሆነሻል?” በማለት አንድ ጊዜ የሚስቱን አንድ ጊዜ የእነ ጸጋዬን ቴአትር በግራ መጋባት ስሜት ውስጥ ሆኖ ይመለከት ጀመር፡፡

በመሃል “ጸጋዬና ጓደኞቹ አንድ አስገራሚ ነገር ይዘውልን መጥተዋል” አለችውና ጸጋዬ ትርዒቱን እንዲቀጥል ነገረችው፡፡ ዳይሬክተሩ መጀመሪያ በማመንታት፣ ዘግይቶ ግን በአድናቆት ቴአትሩን ተመለከተ፡፡ ባየው ነገር የተገረመው ዳይሬክተሩ ቴአትሩ በጃንሆይ ፊት እንዲቀርብ ሙሉ ፈቃድ ሰጠ፡፡

በማግስቱ ጃንሆይ ወደ ትምህርት ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ ከመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር በመሆን ከፊት ለፊት ቁጭ አሉ። አዳራሹ ትንሽ ጨለምለም ተደርጎ የትርኢቱ መጀመር ተበሰረ፡፡ ከዚያ በፊት ማንም የማያውቃቸው ሶስቱ ጓደኛሞች የተለማመዱትን ቴአትር ጢም ብሎ በሞላው አዳራሽ መድረክ ላይ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ተመልካቹም በትዕይንቱ መገረሙን አላቆመም። ጃንሆይና ሌሎች ባለስልጣናትም የወጣቶቹን  ቴአትርና ትወና በመገረም ይመለከታሉ፡፡ ተመልካቹን ሰቅዞ የያዘው የእነ ጸጋዬ ቴአትር ካለቀ በኋላ አዳራሹ በፉጨትና በጭብጨባ ተደበላለቀ። ጃንሆይም በተመለከቱት ትርዒት ተደሰቱ፡፡ እርካታቸውን ለመግለጽ ያህል ጭንቅላታቸውን ላይና ታች ከነቀነቁ በኋላ ለዋና ተዋናዩ ለጸጋዬ ወገግ ያለ ፈገግታ አሳዩት፡፡ ከዚያ ጣታውቸውን በማንቀሳቀስ አንደኛው ጠባቂያቸውን ጠሩትና ጭንቅላቱን ዝቅ አድርጎ ሲቀርብ ንጉሰ ነገስቱ አንዳች ነገር በጆሮው ሹክ አሉትና ፈጥኖ ወደ መድረኩ መጣ። ፈርጣማው አንጋች ሰውዬ ወደ ትንሹ ጸጋዬ ቀርቦ፣ “ጃንሆይ ምን እንዲያደርጉህ ትሻለህ?” ሲል ጠየቀው፡፡

“ማ? እኔ?” ሲል መልሶ ጠየቀው ጸጋዬ።“አዎ አንተ! ጃንሆይ ምን እንዲያደርጉልህ ትፈልጋለህ?”

ምን ምላሽ መስጠት እንዳለበት ትንሹ ጸጋዬ ግራ ገባው፡፡ አጠገቡ ለነበረውና ለሚወደው የጂኦግራፊ መምህሩ “ምን ልበል?” ሲል ጠየቀው፡፡

መምህሩም አሰብ አደረገና “ለትምህርት ቤቱ ትንሽ በጀት እንዲለቀቅ…” ጠይቅ አለው

እንደተባለው ለአንጋቹ ነገረው፡፡ አንጋቹም ሄዶ ለጃንሆይ ነገራቸው፡፡

ጃንሆይም “ለራሱ ለልጁ ተጨማሪ ነገር ምን እንድናደርገለት ይፈልጋል? ሂድና ጠይቀው” አሉት፡፡

አንጋቹ ተመልሶ ጸጋዬን ጠየቀው፡፡

አሁንም ትንሹ ጸጋዬ ግራ በመጋባት ስሜት ጂኦግራፊ መምህሩን ተመለከተው።“ለእያንዳንዱ ተማሪ የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) እንዲሰፋላቸው ልትጠይቅ ትችላለህ” አለው፡፡

ጸጋዬ መምህሩ እንዳሉት መልሶ ለአንጋቹ ነገረው፡፡

አንጋቹም ሄዶ ለጃንሆይ ነገራቸው፡፡

“ፈቅደናል!” በማለት ጃንሆይ መለሱ፡፡

አዳራሹ በጭብጨባ ተናጋ፡፡ ጸጋዬም በኢትዮጵያ የቴአትር መድረክ ለመንገስ የሚያስችለውን የመጀመሪያ ጉዞ አንድ ብሎ መጀመሩን ያስመሰከረበት አጋጣሚ ሆነ፡፡ ጸጋዬም በንጉሰ ነገስቱና በባለስልጣኖቻቸው የተጨበጨበለት፣ የአምቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያኮራ እና ያሸለመ በማለት ዝናው በከተማው ናኘ፡፡ ይሄ ነው የጸጋዬ ጉዞ! ይሄ ነው የጸጋዬ ተሰጥዖ! ይሄ ነው የጸጋዬ ዳና! በዚህ መንገድ አልፎ ነው፤ የኋላ ኋላ አፍሪካዊ ባለቅኔነቱንና ጸሐፌ ተውኔትነቱን ያስመሰከረው፡፡ ‘ዛሬም ድረስ እሱን የሚተካከል ሌላ ጸሃፌ ተውኔትና ገጣሚ የለም!’ እስከሚባል ድረስ በታወቁ ከያኒያን የተጨበጨበለት ጸጋዬ የህይወት ዳራ መነሻው ይሄ ነው፡፡

ጸጋዬን በልጆቹ አንደበት

ጸጋዬ ከልጆቹ ጋር ጥብቅ ትስስር እንደነበረው መጽሐፉን ያነበበ ሰው የማይስተው እውነታ ነው፡፡ ጸጋዬ የሶስት ሴቶች አባት ነው፡፡ በጣም የሚወዳት ሚስቱ ላቀች ከቀድሞ ባሏ የወለደቻቸው ሁለት ወንድ ልጆች፣ እንደ ራሱ አብራክ ክፋይ አድርጎ እንደ አባት ሆኖ አሳድጓል። ወጣቱ ጸጋዬ ሚስቱ ወይዘሮ ላቀች አግብታ የፈታች፤ የሁለት ልጆች እናት መሆኗን ከመጤፍ ሳይቆጥር በሙሽራ ደንብ አግብቷት እስከ ህይወቱ ፍጻሜ ድረስ በፍቅር አብሯት ኖሯል፡፡ መጽሐፉ ውስጥ እንደሰፈረው ጸጋዬ ለፈጠራ ሥራዎቹ መቃናትና በተመስጦ እንዲሰራ ካስቻሉት ነገሮች አንዱ የሚስቱ ሚና ትልቅ ድርሻ ይወስዳል፡፡

እንደ ባለቅኔ ሳይሆን እንደ አባት ጸጋዬን በልጆቹ አንደበት ልጁ ዮዲት ጸጋዬ እንዲህ ስትል ስለ አባቷ መጽሐፉ ውስጥ አስፍራለች፤ “አባታችን እንደ ጓደኛ የቆርኪ ቡናችንን እየጠጣ፤ ስንዘል እንደ አጫዋችም እንደ ተጫዋችም ሆኖ በኪሱ የያዛቸው ሳንቲሞች እስኪዘረገፉ አብሮን ይዘል ነበር፡፡ ከፍ ካልንም በኋላ ፓርቲ ለመውጣት (ከጓደኞቻችን ጋር ለመዝናናት)  ከእናታችን ቁም ሳጥን ያለ ፈቃድ ልብስ ስንወስድ ከእኛ ጋር ተባብሮ ምስጢራችንን ይደብቅልናል፡፡

“በየዓመቱ በትንሳዔ በዓል ሌሊት ከተኛበት ውሃ አርከፍክፎ ከእንቅልፋችን ቀስቅሶን እንደ ልጅ መደሰቱ ሌላ የልጅነት ትውስታችን ነው፡፡ አንዳንዴ የለመደውን ለማድረግ ከመኝታ ቤታችን ሲገባ ነቅተን ካገኘን ተንኮሉ ባለመሳካቱ ይቆጭና የያዘውን ውሃ ቸልሶብን ከእኛ ጋር አብሮ ይስቃል” በማለት ዮዲት (በገጽ፣2) ከአባታቸው ጋር የነበራቸው መስተጋብር አስፍራለች፡፡

አብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review