መንግስት ሕዝብን የሚያከብር፤ የሚያዳምጥ እና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ማረጋገጣቸውን በሕዝባዊ ውይይት የተሳተፉ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ነዋሪዎች ተናግረዋል ።
“የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግስት ትሩፋቶች!” በሚል ርዕስ ከባለፈው ሳምንት የቀጠለ ሕዝባዊ ውይይት በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 4 ተካሂዷል ።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ የጉለሌ እፅዋት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጉተማ ሞረዳ (ኢ/ር) በአዲስ አበባ ከተማ ከለውጡ ወዲህ በርካታ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አንስተው ለስኬቱም የከተማ አስተዳደሩ አመራር ከነዋሪው ጋር በጋራና በቅንጅት በመስራቱ የተመዘገበ ድል መሆኑን ገልፀዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ከዚሕ ቀደም አስተዳደሩ ይሄን መሠል ሕዝባዊ ውይይቶች ሲያካሂድ የቆየ መሆኑን አንስተው መድረኩ ተለዋዋጭ በሆነው ቀጣናዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።

የክ/ከተማው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊና የብልፅግና ፖርቲ ምክትል ኃላፊ አቶ ሲሳይ ኬኔ ሕዝባዊ ውይይቱ ነዋሪው የሚያነሳቸውን ችግሮች በአግባቡ ለመለየት እና ለመፍትሔው በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል ።
በመድረኩ ለውይይት የተዘጋጀ ሰነድ በወረዳው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ማርታ ተፈራ የቀረበ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተከናወኑ ሰው ተኮር ተግባራት የቀረቡ ሲሆን ከዚህ ቀደም ነዋሪው ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችና የተፈቱበት አግባብ ያካተተ ነበር ።

ተወያዬችም በከተማ አስተዳደሩ የተሠሩ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን አድንቀው አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም ነዋሪው ያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችን በእቅድ አካቶ ምላሽ የሰጠበትን ፈጣን ሂደት እደንቃለን ብለዋል።

ይህም መንግስት ለሚመራው ሕዝብ ያለውን ክብር ያሳየ፤ እንደ ሃገር ካለንበት ችግር ለማላቀቅ ቁርጠኛ እንደሆነ ማረጋገጫ የሰጠበት ነው ሲሉ ተወያዮቹ አንስተዋል።
የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራ አሁንም ሊጠናከር ይገባል ወደ እኛም ሊመጣልን ይገባልም ያሉት ተወያዬቹ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የወሰዳቸው እርምጃዎች በተጨባጭ ለውጥ ያመጡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከግምት ያስገቡ ናቸው ብለዋል።

ተወያዮቹ በተለይም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለሚሰጡት አመራር አድናቆት የቸሩ ሲሆን የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ፣ የትምህርት ቤቶች ምገባ እንዲሁም ከተማዋ በአለም አቀፍ መድረኮች እያገኘችው ያለውን እውቅና እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ለተገኙ መሻሻሎች ምስጋና አቅርበዋል።

ነዋሪዎቹ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሏቸውን ኃሳቦች ያነሱ ሲሆን እንደወረዳ የመንገድ ዳር መብራት እና የውሃ መቆራረጥ እንዲሁም የወጣቶች ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት ሊፈታልን ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል ።
መድረኩንም የመሩት አወያዮች እንደከተማ የመጡ ለውጦችን አንስተው አሁንም እንደወረዳ ያሉ ችግሮችን ሕዝቡን ባሳተፈ መንገድ በእቅድ እንደሚፈቱ ተናግረዋል።
በታምሩ ደምሴ