“ውብ አዲስ” ተከታታይ ድራማ ከልዩ ዕድል እና የሚሊዮን ብር ሽልማት ጋር መጣ‎

You are currently viewing “ውብ አዲስ” ተከታታይ ድራማ ከልዩ ዕድል እና የሚሊዮን ብር ሽልማት ጋር መጣ‎

በኢትዮጵያ የፊልም ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያሳረፈው አንጋፋው የፊልም ሰው ቴዎድሮስ ተሾመ፣ “ውብ አዲስ” የተሰኘ ታላቅ ፕሮጀክት ይፋ አድርጎታል። ይህ ፕሮጀክት እንደተለመዱት አይነት የቴሌቪዥን ድራማ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ኮከቦች የሚፈሩበትና የጥበብ ባለሙያዎች ሕይወት የሚቀየርበት አዲስ ምዕራፍ ነው።

የታላቁ ፕሮጀክት መጀመሪያ

ቴዎድሮስ ተሾመ በኢትዮጵያ የፊልም ታሪክ ውስጥ በተለይም በ“ሶስት ማዕዘን” እና በቅርቡ በ“ዝምታዬ” ፊልሞቹ ደማቅ አሻራን አሳርፏል። ‎አሁን ደግሞ ለሁለት አሰርት ዓመታት በልቡ ሲኣወጣና ሲያወርደው የቆየውን ሀሳቡን በተግባር መሬት ላይ ሊያወርደው በሙሉ አቅምና ወኔ ተመልሷል። ለዚህ ሕልሙ ዕውን መሆን ደግሞ ሁነኛ አጋር ያደረገው የትውልዱ ድምጽ የሆነውንና በየጊዜው እንደስሙ አዲስ እየሆነ የመጣውን አዲስ ሚዲያ ኔትወርክን ነው።

‎ታኅሣሥ 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ፒያሳ በሚገኘው የአራዳ ፓርክ በአንድ ወገን የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የማናጅመንት አባላት በሌላ በኩል ደግሞ የፊልም ሰው ቴዎድሮስ ተሾመ አብረውት ከሚሠሩ ባለሙያዎች ጋር አንድ ላይ ሆነው ስለታቀደው ሥራ ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል።

‎ለዚህ በአይነቱ ለዬት ላለ ፕሮጀክት በሩን ከፍቶ የተበቀው አዲስ ሚድያ ኔትወርክ ተመልካችን ለማርካት ቁርጠኛ መሆኑንና ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ለማቅረብ ማናጅመንቱ መወሰኑን ያረጋገጡት ደግሞ ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ካሳሁን ጎንፋ ናቸው።

“ውብ አዲስ” ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?

በአዲስ ሚድያ ኔትወርክ በኩል ለተመልካች ሊደርስ የተወጠነው አዲሱ የተከታታይ ድራማ (በአዘጋጆቹ አገላለጽ ተከታታይ ፊልም) ፕሮጀክት 4 ሲዝኖች እና 52 ክፍሎች ያሉት ሲሆን አቀራረቡም በሁለት ትይዩ ታሪኮች (Parallel Plot) የተዋቀረ በመሆኑ ተመልካችን በጉጉት እንዲጠብቅ የሚያደርግ (Suspenseful) እንደሚሆን ይጠበቃል።

‌‎የዚህ ድራማ ተዋንያን ስም እና ዝና ያተረፉ ተዋንያን ብቻ አይደሉም፤ ከእነርሱ እኩል አዳዲስ ተዋንያንም ወደመድረኩ የሚመጡ መሆናቸውና ለዚህም ልዩ የምልመላ መንገድ መቀየሱ ልዩ ያደርገዋል።

‎ቴዎድሮስ ለወጣት ባለተሰጥዖዎች መልእክት አስተላልፏል “ቀበቷችሁን ጠበቅ አድርጋችሁ መልካም ዜና ጠብቁ፤ ሕዝብ እያያችሁ፥ በችሎታችሁ ብቻ ለትወና የምትመረጡበት መደላድል ተመቻችቷል” ነው ያለው።

የሚሊዮን ብር ዕድል ለወጣት ባለተሰጥዖዎች

‌‎የ“ውብ አዲስ” ጥራት የተረጋገጠው ለ20 ዓመት ብቻ ስለታሰበበት ሳይሆን በሥራው ላይ በተሰለፉት አንጋፋ ባለሙያዎችም ጭምር ነው። ለዚህ አንዱ ማሳያ የሾው ራነር ሆኖ የሚሠራው ተስፋዬ እሸቱ (‎ረዳት ፕሮፌሰር) በቡድኑ ውስጥ መካተቱ ሲሆን ውድድሩ የተመልካችን ስሜት የሚቆጣጠርና አዳዲስ ፊቶችን ወደ አደባባይ የሚያወጣ እንደሆነ እርሱም ያለውን ዕምነት ገልጿል። ሌላኛው ጉምቱ የፊልም ሰው ‎ተስፋዬ ሲማ ደግሞ ተዋንያኑ ከመተወናቸው በፊት ጥበብን በሥነ-ስርዓቱ እንዲቀስሙ ልዩ የትወና ስልጠና ይሰጣል።
‎በዚህ የተዋንያን የውድድር ውስጥ ተሳትፈው አሸናፊ የሚሆኑት እስከ 1,000,000 (አንድ ሚሊዮን) ብር የሚያሸለሙ ሲሆን፣ ከገንዘቡ ባሻገር በድራማው ላይ በመሪ ተዋናይነት የመሳተፍ ወርቃማ ዕድልንም ያስገኛል።

እንዴት መመዝገብ ይቻላል?

‎እንግዲህ የጥበብ ናፍቆት ያላችሁ፥ ዕድል ፊቷን ወደእናንተ እንድታዞር የምትፈልጉና ተሰጥዖ እያለኝ ዕድሉን አታሁ ብላችሁ ለምትቆጩ ሁሉ የ1 ሚሊዮን ብር ሽልማት እና በዝና ማማ ላይ ኮከብ የምትሆኑበት በር ተከፍቷልና ሳይረፍድ ፈትናችሁ ተመዝገቡ።

ለ“ውብ አዲስ” ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ እና የተዋንያን የተሰጥዖ ውድድር ለመመዝገብ ከቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ፊትለፊት በሚገኘው ራንዴቩ ሕንጻ 5ኛ ፎቅ በቴዲ ስቱዲዮ በአካል በመምጣት እንድትመዘገቡ እየጠበቅናችሁ ነው።

ዛሬ ተመዝጋቢ ለመሆን የምትመጡበት “ውብ አዲስ” ላይ ነገ ደግሞ ‎ስመ-ጥር ተዋንያንና ተዋናይት አዳዲስ ባለተሰጥዖዎች የሚገናኙበት ፣ የኢትዮጵያን የቴሌቪዥን ድራማ ታሪክ አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚያራምደው ይጠበቃል።

‎የተዋናዮች ምዝገባው ከታኅሣሥ 8 ጀምሮ እስከወሩ መጨረሻ ቀን ድረስ ይካሔዳል ፤ ያሉት ቀናት እንዳያልፏችሁ ተጠቀሙባቸው እያልን ለተመዝጋቢዎች በሙሉ መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review