በልብ ወለድ እና በነባራዊ ገጸ-ባህሪያት መስተጋብር የሚተረክ “የኢትዮጵያ የስንዴ ሽግግር” (Ethiopia’s Wheat Transformation) የተሰኘ ፈጠራ የታከለበት ዘጋቢ ፊልም ተመርቋል።
ፊልሙ በሎስ አንጀለስ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሰራ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በግብርና ራስን የመቻል አስደናቂ ጉዞዋን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ፊልሙ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ታሪካዊ የስንዴ አብዮት ላይ ያጠነጠነ ሲሆን፣ ዮሐንስ የተባለ ልብ ወለድ ገጸ-ባህሪ በኦሮሚያ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች የሚገኙ መንገዶችን እና ሰፊ የእርሻ መሬቶችን ሲያቋርጥ ይታያል።

ዮሐንስ ሀገርን የሚመግብ እና የወደፊት ተስፋን የሚሰንቅ ምርት የጫነውን ግዙፍ የጭነት መኪናውን እያሽከረከረ ፣ በመንገዱ ላይ እውነተኛ ታታሪ አርሶ አደሮችን ያገኛል።
በአፍሪካ ትልቁ የስንዴ አምራች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ በእርጋታ ነገር ግን ጥልቅ የሆነ የእድገት ሽግግር ውስጥ ስትገባ፣ ታሪኩ ከዚህ ዕድገት ጀርባ ያለውን የሰው ልጅ ብርታት ገልጦ ያሳያል።
“የኢትዮጵያ የስንዴ ሽግግር” ማራኪ የመልክዓ ምድር እይታዎችን ከቅርብ የታሪክ አተራረክ ጋር በማዋሃድ፣ አርሶ አደሮች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከሚጠቀሙባቸው የገጠር እርሻዎች አንስቶ በምርታቸው እስከሚተዳደሩት ሥራ የሚበዛባቸው የከተማ ማዕከላት ድረስ ይወስደናል።
ፊልሙ ስለ ስንዴ ከመተረክም በላይ፣ የጽናትን፣ የፈጠራን እና ራስን ወደ መቻልና ወደጋራ ብልጽግና የምትገሰግስን ሀገር የሚያሳይ ምስል ነው።