የኢትዮጵያና የሕንድ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መጠናከር ሌሎች ሀገራት የኢትዮጵያን ተፈላጊነትና ቁልፍ ሚና እንዲገነዘቡ የሚያስችል መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
አምባሳደሩ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የሁለቱ ሀገራት የቆየ ግንኙነት አሁን ላይ ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩንና ይህም የአፍሪካ-ሕንድ ግንኙነትን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያና ሕንድ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የታሪክና የንግድ ትስስር ያላቸው ሲሆን፣ በዘመናዊ ዲፕሎማሲ ደግሞ ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ጠንካራ ወዳጅነት መስርተዋል።
ሕንድ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቁልፍ የልማት አጋር አድርጋ እንደምትመለከት የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ ይህ ከልብ የመነጨ ወዳጅነት አሁን ላይ በግብርና፣ በማዕድን፣ በማኑፋክቸሪንግና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ሰፊ ስትራቴጂካዊ ትብብር እየተፈጠረበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሁለቱ ሀገራት የብሪክስ (BRICS) አባል መሆናቸውና የጋራ የልማት ግቦችን መጋራታቸው፣ በዓለም ደቡባዊ ቀጣና (Global South) ውስጥ ያሉ ሀገራትን ተጽዕኖ ለማሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ተገልጿል።
በተለይም እንደ ብድር ቅነሳ ያሉ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ለማጠናከር የሁለቱ ሀገራት ሚና ከፍተኛ አምባሳደር ዲና በአጽንዖት ተናግረዋል።
ሕንድ ለኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዋና ምንጭ ከመሆኗም ባለፈ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ባሉ መምህራን አማካኝነት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ መጠናከሩንም ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጉብኝትም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት የሚያሳይና የኢኮኖሚ ትስስሩን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑንም ገልጸዋል።
በመጨረሻም፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረጉ ስምምነቶች ተጨባጭ ፍሬ እንዲያፈሩ በትኩረት መተግበር እንደሚገባ አምባሳደሩ አሳስበዋል።
ይህ በትኩረት የመስራት ልምድ ለወደፊቱ ተጨማሪ የኢንቨስትመንትና የልማት ስምምነቶች እንዲመጡ በር የሚከፍትና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት የሚያፋጥን መሆኑንም ገልጸዋል።
በሄለን ጀንበሬ