በሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ሊፈፀሙ የሚችሉ ታሪኮች

You are currently viewing በሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ሊፈፀሙ የሚችሉ ታሪኮች

AMN ታኅሣሥ 13 ቀን 2018 ዓ.ም

ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ የምታሰናዳው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ትናንት በይፋ ተጀምሯል፡፡ አዘጋጇ ሀገር ኮሞሮስን 2ለ0 በማሸነፍ የተጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በርካታ ጉዳዮች ይጠበቃሉ፡፡

ዘ አትሌቲክም ደማቅ እንደሚሆን ከተገመተለት የዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ሊፈፀሙ ይችላሉ ያላቸውን ታሪኮች በድረገፁ አስፍሯል፡፡

ሞሐመድ ሳላህ በመጨረሻ የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳ ይሆን?

ሞሐመድ ሳላህ ሰባት ጊዜ ዋንጫ አንስታ የአህጉሩ የበላይ ለሆነችው ግብፅ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ የ33 ዓመቱ የሊቨርፑል ኮከብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክለቡ ጥሩ ጊዜ ባያሳልፍም ግብፃውያን በእርሱ ተስፋ አላቸው፡፡

ሳላህ ለብሔራዊ ቡድንም ይሁን ለተጫወተባቸው ክለቦች ካበረከተው አስተዋፅኦ መነሻ አፍሪካ ካፈራቻቸው ድንቅ ተጫዋቾች መሀል ይመደባል፡፡ ይህን ታላቅነቱን የበለጠ ለማግዘፍ ግን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማንሳት እንዳለበት ይነገራል፡፡ ለሳላህ ምናልባት የዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻው ሊሆን ይችላል፡፡

እኤአ ከ2011 ጀምሮ ሀገሩን እያገለገለ የሚገኘው ሳላህ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ያስመዘገበው ትልቁ ውጤት በ2017 እና 2022 በአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ደርሶ ዋንጫ ያጣባቸው አጋጣሚዎች ናቸው፡፡

በቀጣይ ነሐሴ ወር 34ኛ ዓመቱን የሚይዘው ሞሐመድ ሳላህ ሀገሩን ለሁለት የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ቢያበቃም የአፍሪካ ዋንጫ ማንሳታ ስሙን ዘላለማዊ ያድርግለታል፡፡

ኮትዲቯር በተከታታይ ለመንገስ ትወዳደራለች

ኮትዲቯር የ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድርን አሰናድታ ዋንጫውን በሀገሯ ያስቀረችበት ታሪክ አስደማሚ ነው፡፡ ሀገሪቱ ውድድሯን ጊኒ ቢሳውን በማሸነፍ ብትጀምርም ሁለት ተከታታይ የምድብ ጨዋታዎቿን ስትሸነፍ በተስፋ መቁረጥ ዋና አሰልጣኟን ዦን ሊውስ ጋሴን አሰናበተች፡፡

ሦስት ነጥብ እና ሦስት የግብ እዳ የነበረባት ኮትዲቯር ግን ከምድባቸው ጥሩ ሦስተኛ በመሆን ጥሎማለፉን ከተቀላቀሉ አራት ሀገራት አንዷ ሆነች፡፡ ለማመን የሚከብደው ታሪኳንም አሁን ብሔራዊ ቡድኑን እየመራ በሚገኘው ኤመርስ ፋዬ አማካኝነት መስራት ጀመረች፡፡

ዝሆኖቹ ሴኔጋል ፣ ማሊ ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እንዲሁም በፍፃሜው ናይጄሪያን በመርታት ልብ ወለድ የመሰለ እውነተኛ ታሪክ አስከተቡ፡፡

ከሁለት ዓመት በኋላ ለሌላ የአፍሪካ ዋንጫ ድል ሞሮኮ የከተሙት ኮትዲቯሮች ከማንም ጋር መፎካከር የሚችል ስብስብ አላቸው፡፡ ጥያቄው ዋንጫውን በድጋሚ ማንሳት ይችላሉ ውይ? የሚለው ነው፡፡

ሁሌም ግምት የሚሰጣት ናይጄሪያ ዘንድሮስ?

ናይጄሪያ ካላት ከዋክብት መነሻ የምታስመዘግበው ውጤት ደጋፊዎቿን የሚያበግን ነው፡፡ በተለይ በቅርቡ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ያስመዘገቡት ውጤት በርካቶችን አስቆጥቷል፡፡ የኢንተር ኮንቲኔንታል የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ለመሳተፍ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ተጫውታ አለማሸነፏ እንደ ትልቅ ውድቀት ተቆጥሯል፡፡

ተጫዋቾቹም ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ ከሀገሪቱ ፌዴሬሽን ጋር ንትርክ ውስጥ መግባታቸው ደጋፊዎቹን ይበልጥ አበሳጭቷል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የተከፋውን ደጋፊ የሚክሱበት አጋጣሚ አግኝተዋል፡፡ በማሊያዊው የ48 ዓመት አሰልጣኝ ኤሪክ ቼሊ የሚመሩት ንስሮቹ ቪክቶር ኦሲምኸን ፣ አዴሞላ ሉክማን ፣ አሌክስ ኢዎቢ ፣ ካልቨን ባሲ የመሳሰሉ ኮከቦችን ይዘዋል፡፡

ናይጄሪያ ለመጨረሻ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳችው ከ12 ዓመታት በፊት በ2013 ነበር፡፡

የአዘጋጇ ሀገር ሞሮኮ የዋንጫ ተስፋስ?

ሞሮኮ በ2022ቱ የኳታር ዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ደርሳ ለአፍሪካ አዲስ ታሪክ ካስመዘገበች በኋላ ዓይን በዝቶባታል፡፡ ዘንድሮ ያዘጋጀችውን የአፍሪካ ዋንጫ በሀገሯ እንድታስቀር ይጠበቃል፡፡

በበርካታ ደጋፊዎቿ መታገዟ ብቻ ሳይሆን ያላት የስብስብ ጥራት ከ49 ዓመት በኋላ የአህጉሪቱ ቁንጮ እንድትሆን ያስችላታል ተብሏል፡፡ ሞሮኮ ለመጨረሻ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳችው 1976 በኢትዮጵያ በተዘጋጀው ውድድር ላይ ነበር፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review