በአሜሪካ ፍሎሪዳ ለሚከናወነው የዓለም ሀገር አቋራጭ የአትሌቲክስ ውድድር ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
በ10 ኪ.ሜ አዋቂዎች ፣ በ6 ኪ.ሜ ወጣቶች እና በድብልቅ ሪሌ በአጠቃላይ በ5 ዘርፎች ኢትዮጵያን የሚወክሉት አትሌቶቹ በሆቴል በመሰባሰብ በትራክ እና በሱልልታ ሜዳ ልምምድ እያደረጉ ይገኛል።
ጃን ሜዳ ላይ በነበረው የሀገር አቋራጭ ውድድር በሁለቱም ፆታ 32 አትሌቶች ተመርጠው በዝግጅት ላይ ሲሆኑ ከዚህ በፊት ከተመዘገቡት ውጤቶች በበለጠ ሜዳልያ ለማምጣት በጥሩ ስነ ልቦና ላይ እንደሚገኙ አትሌት ቢኒያም መሀሪ እና አትሌት ሂሩት መሸሻ ከኤኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
በመግባባት እና በመነጋገር የቡድን መንፈሱን ለማምጣት እየሰራን ነው ሲሉም አትሌቶቹ አክለዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የምትታወቅበት የአትሌቲክስ ውጤት የጠፋው የቡድን ስሜቱ በመሸርሸሩ ነው የሚሉት ደግሞ አሰልጣኝ ሁሴን ሽቦ እና ቶሎሳ ቆቱ ስሜቱን በማምጣት በውጤቱ የተከፋውን ህዝብ ለመካስ በጥሩ ዝግጅት ላይ ነን ብለዋል።
በ45ኛው የሀገር አቋራጭ ውድድር በሴቶች ከተመዘገበው ወርቅ ውጭ ሌላ አለመኖሩ አጥጋቢ አልነበረም የሚሉት አሰልጣኞቹ ያንን ለመቀየር ወደ አሜሪካ እንጓዛለን ሲሉ ተናግረዋል።
በሀገር አቋራጭ ውድድር ከግል በተጨማሪ በቡድን ውጤት ከመጣ ሜዳልያ ይገኝበታል የሚሉት አሰልጣኞቹ አትሌቶቹን በአንድነት በመስራት የጋራ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከስልጠናው በተጨማሪ በምክርም እንደሚያግዟቸው ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።
አልማዝ አዳነ