ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በማሳካት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልፅግና ማፋጠን ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ

You are currently viewing ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በማሳካት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልፅግና ማፋጠን ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ

AMN – ታኀሣሥ 14/2018 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍና ህብረተሰቡ በመተባበር ከሰሩ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በማሳካት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልፅግና ማፋጠን እንደሚቻል ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብሔራዊ የዲጂታል ትራስፎርሜሽን ምክር ቤት ሊቀ መንበር ተመስገን ጥሩነህ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማጠናቀቂያ እና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ይፋዊ ማስጀመሪያ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ሥልጠና መርሐ ግብር በመተግበሩ እስካሁን ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በመላው ሀገሪቱ የሰለጠኑ መሆኑን እና 1 ነጥብ 9 ሚሊዮኑ ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል። ።

ይህም የዲጂታል አጠቃቀም ብቃትን ለመጨመርና ሰው ተኮር ልማትን ለማጠናከር ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

የ«ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025» ትግበራ በይፋ ተጠናቆ ሀገሪቱ ወደ «ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030» አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሯንም አብስረዋል።

ይህ ስትራቴጂ የፋይናንስን፣ የአገልግሎት አሰጣጥን፣ የንግድን፣ የመንግስት ተደራሽነትን፣ የፀጥታና የሚዲያ አውዶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማሻሻል የሚያስችል ነው ብለዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን እንደሚሰራ አብራርተዋል።

የዲጂታል ሥራን በትኩረት በመስራት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከ68 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያልተገባ ወጪን ማስቀረት ተችሏል።

መንግስት፣ የግሉ ዘርፍና ህብረተሰቡ በመተባበር ከሰሩ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በማሳካት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማፋጠን እንደሚቻልም ጠቅሰዋል።

በበረከት ጌታቸዉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review