AMN ታኅሣሥ 14 ቀን 2018 ዓ.ም
እስካሁን 47 የፈጠራ ስራዎችን የሰራው ወጣት ፌደሳ ሹማ፤ እ.ኤ.አ በ2007 በቻይና ቲያንጂን ከተማ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ የኤሌክትሪክ ችግርን የሚፈታ የፈጠራ ስራውን አቅርቦ ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም ደግሞ 9ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ፈደሳ ሹማ ከAMN ዲጂታል ጋር በነበረው ቆይታ እንደገለጸው፤ “ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኙት 48 በመቶ ብቻ ናቸው። በመሆኑም በጨለማ ውስጥ ለሚኖሩት 52 በመቶ የገጠር ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ችግር መፍትሄ እንዲሆን ይህንን ልዩ የፈጠራ ስራ ለሥራ አብቅቻለሁ” ብሏል።

የፈጠራ ስራው “Power Generator” (የኃይል ማመንጫ) ይሰኛል። መሣሪያው ለአንድ ሰዓት ያህል ቻርጅ ከተደረገ ለ24 ሰዓታት 50 አምፖሎችን ማብራት ይችላል። ለስድስት ሰዓታት ቻርጅ ከተደረገ ደግሞ ለአንድ ወር ያህል ያለ መቆራረጥ አገልግሎት ይሰጣል። ፈደሳ አክሎም መሣሪያው ራሱን በራሱ ቻርጅ የማድረግ ብቃት እንዳለው ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፈጠራ ስራውን አራት ጊዜ ያህል የተመለከቱ ሲሆን፣ ምርቱ በስፋት ቢመረት ውጤታማ እንደሚሆን አረጋግጠውለታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ፦ “ይህ ፈጠራ በጣም አስገራሚ ነው፤ ለአንድ ሰዓት ብቻ ቻርጅ ተደርጎ እስከ 50 አምፖሎችን ለ24 ሰዓት ማብራት ይችላል፣ ድምፅ የለውም፣ ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም አለው፤ የገጠርና የከተማን ችግር በደንብ ይፈታል” ማለታቸው ተገልጿል።
በትውልድ አካባቢው በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ እንደሆነ የተናገረው ፈደሳ፤ በአሁኑ ወቅት የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፣ በፈጠራ ስራው ላይ ተሰማርቶ “Fedhoo Power Solution” የተባለ ድርጅት በማቋቋም በዋና ስራ አስኪያጅነት እየመራ ይገኛል።

ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የፈጠራ ስራዎችን የጀመረው ፈደሳ፤ በ2009 ዓ.ም በመቀሌና በአክሱም በተካሄዱ ውድድሮች ማሸነፉን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል። በ2015 ዓ.ም በ“ብሩህ ኢትዮጵያ” የፈጠራ ውድድር አሸናፊ እንደነበረም አስታውሷል።
ፈደሳ በኢትዮ-ቻይና ፌዴራል ቲቪኢቲ (TVET) በመግባት ጥሪ ከተደረገላቸው 548 ሰዎች መካከል የሙያ ብቃቱን አረጋግጧል። በአሁኑ ወቅት “Fedhoo Power Solution” በሚል የድርጅት ፈቃድ አግኝቶ ምርቱን ወደ ገበያ ያወጣ ሲሆን፣ በርካታ ደንበኞችን በማፍራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ትዕዛዞችን ተቀብሎ እያመረተ እንደሚገኝ ተናግሯል።

በኢሉ አባ ቦር ዞን መቱ ከተማ “ገንዶሴ” በተባለ ቀበሌ የኤሌክትሪክ መስመር በመዘርጋት 150 አባወራዎችን ተጠቃሚ ማድረጉንም ገልጿል። ፈደሳ ከኃይል አቅርቦት ባለፈ ለገበሬዎች ምርታማነትን የሚጨምሩ፣ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ የመጠጥ ውሃና የመንገድ ችግሮችን የሚፈቱ፣ ለሆስፒታሎችና ለላቀ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እገዛ የሚያደርጉ የፈጠራ ስራዎችን ማከናወኑን ጠቁሟል።
በተጨማሪም የሦስት ትልልቅ ድርጅቶች እቅድ በእጁ ላይ እንዳለ ጠቅሶ፣ ያለምንም የኤሌክትሪክ ባትሪ የሚሰራ ተሽከርካሪ የመስራት ሙከራው 30 በመቶ ላይ መድረሱን ገልጿል።
በደራርቱ ተሬሳ