የሳንባ ምች በሽታ በቫይረስ፣ በባክቴሪያ ወይም በፈንገስ አማካኝነት የሚከሰትና አብዛኛውን ጊዜ በመተንፈሻ አካላት ጤና መታወክ የሚቀሰቅስ አጣዳፊ የሳንባ ሕመም ነው፡፡
የሳንባና የጽኑ ሕሙማን ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር አምሣሉ ቢተው ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በሽታው በተለይ በባክቴሪያ አማካኝነት የተከሰተ ከሆነ በቀላሉ ወደ ጽኑ የሳንባ ምችነት የመቀየር ዕድሉ ከፍተኛ ነው።

በሳንባ ውስጥ በቂ አየር መዘዋወር ሳይችል ሲቀር የሚፈጠር እርጥበት ለበሽታው መከሰት ዋነኛ መደላድል እንደሚፈጥርም ባለሙያው አብራርተዋል።
እንደ ኩፍኝ፣ ትክትክ፣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ብሮንካይትስ እና አስም ያሉ በሽታዎች ለሳንባ ምች መከሰት መንገድ ከፋች መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር አምሣሉ፤ በተለይም ህፃናት፣ በእድሜ የገፉ እና በደማቸው ውስጥ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

ለመተንፈስ መቸገር፣ ከላይ ከላይ መተንፈስ፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ማቃሰትና የደረት ውጋት፣ ፊትና ከንፈር አካባቢ ሽፍታ መውጣት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ የሚሄድ ሳል እና የራስ ምታት የሕመሙ ምልክቶች ናቸው።
አራስ ልጆች፣ አረጋውያን እና በሽታ የመከላከል አቅማቸው ደካማ የሆኑ ሰዎች ትኩሳት ሳይኖራቸው በሳንባ ምች ሊጠቁ ስለሚችሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ መክረዋል።
በሽታውን ለመከላከል ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ሲጃራ አለማጨስ እንዲሁም እንደ አስም፣ ስኳርና የልብ ሕመም ያሉ ተጓዳኝ በሽታዎችን በአግባቡ መቆጣጠር እንደሚገባ ገልፀዋል።
ሕመሙ ከተከሰተም በኃላ በወቅቱ በሚደረግ የሕክምና ክትትል፣ በፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒቶችና በኦክሲጅን ቴራፒ ማገገም እንደሚቻል ዶ/ር አምሣሉ ቢተው አረጋግጠዋል።
በበረከት ጌታቸው