አዲሶቹ መሠረተ ልማቶችና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትንሳኤ

You are currently viewing አዲሶቹ መሠረተ ልማቶችና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትንሳኤ

AMN-ታኀሣሥ 23/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ እየተዘረጉ ያሉ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች፣ ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገሩት ይገኛሉ። በተለይም አዳዲስ መንገዶች፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና ማራኪ ሪዞርቶች መገንባታቸው ለኢንዱስትሪው አዲስ ሕይወት መዝራቱ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ያሏት ታሪካዊ ቅርሶችና አስደናቂ የተፈጥሮ መስህቦች ቀደም ሲል በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ተደራሽነታቸው ውስን የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን እየተገነቡ ባሉ ዘመናዊ መንገዶች አማካኝነት ቱሪስቶች ያለምንም እንግልት መዳረሻዎቻቸውን እንዲጎበኙ ዕድል ፈጥሯል።

ይህ የመድረስ ቀላልነት የጎብኚዎችን ቁጥር ከመጨመሩም በላይ የቆይታ ጊዜያቸውን የሚያራዝም ሆኖ ተገኝቷል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ይህ የቱሪዝም መነቃቃት ከዘርፉ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ሲሆን ሀገሪቱ ከቱሪዝም የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ድንቅ ባህሎችና እሴቶች በዓለም አቀፍ መድረክ ጎልተው እንዲታዩና እንዲታወቁ ሰፊ ዕድል እንደከፈተም ተገልጿል፡፡

በሀገሪቱ እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የታሪክን ጥንታዊነት ከዘመናዊነት ምቾት ጋር በማጣመር፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እያደረጓት ነው፡፡ ይህም ሀብትን ከማበልጸግ ባለፈ የሀገርን ገጽታ በመገንባት ረገድ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ታምኖበታል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review